የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-3 ፋሲል ከነማ

“የጌታነህ ወደ ጎል መቅረብ ግን የበለጠ ቡድኑን የሚያነሳሳ ነው” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

“ማሻሻል ያለብንን ነገሮች እያሻሻልን አልመሰለኝም” አሰልጣኝ አስራት አባተ

አፄዎቹ ከዕረፍት መልስ ባስቆጠሯቸው ሦስት ጎሎች ድሬዳዋ ከተማን ከረታበት ጨዋታ መቋጫ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞች ጋር ቆይታን አድርጋለች።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫን ወስደው ስላሸነፉበት ጨዋታ…

“ጠንካራ ጨዋታ እንደሚሆን ከመጀመሪያም ገምተን ነበር ግን ከሌላው ጊዜ በተሻለ የማሸነፍ መንፈስ ነው ወደ ሜዳ የገባነው ፣ ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ነገር ግን ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት ስለሆነ የተመለስነው ተጫዋቾች ላይ መጠነኛ ጫና እንደነበር ያስታውቃል። በመጀመሪያ አርባ አምስት ብልጫ በነበረን ሰዓት ራሱ ተጋጣሚ የግብ ክልል ጋር የምናገኛቸውን ኳሶች በቀላሉ ነበር የምናበላሻቸው ወደ ሙከራነት ከመቀየራቸው በፊት ነበር የሚባክኑት ስለዚህ ከዕረፍት በኋላ ያደረግነው ምንድነው ያንን በዛው የጨዋታ መንገድ ውስጥ ሆነን የምናገኛቸውን ዕድሎች ወደ ተሻለ ዕድል ለመቀየር ነው ጥረት ያደረግነው ፣ በተለይ የጌታነህ ጎል ከመቆጠሩ ከቅጣት ምቱ በፊትም ተደጋጋሚ ዕድሎችን ማግኘት ችለን ነበር ፣ ስለዚህ ያቺ ትንሽ ማስተካከያ ጎል የማግባት ችግራችንን ሊቀርፍልን ችሏል። ከዛ በላይ ግን በሙሉ የጨዋታ ሰዓት ለማሸነፍ እና ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሄድንበት መንገድ የተሻለ ነበር።”

ሽመክት ጉግሳ ከዕረፍት መልስ ወደ ኋላ ተስቦ ስለ መጫወቱ እና ስለ ፈጠራቸው ሁለት የጎል ዕድሎች…

“በዕርግጥ የመጫወቻ ሜዳውን በተለይ እነርሱ ወደ ኋላ ድሮፕ አድርገው ከመጫወታቸው አንፃር ክፍተቶች አልነበሩም ፣ እነዛን ክፍተቶች ልናገኝ የምንችለው በመስመሮች መሐል ላይ ኳስን የሚቀበል ሰው መፍጠር ነበር እና ሽመክት ያደረገው ያንን ነው። በተከላካይ እና በመሀከል የነበረውን ክፍተት ነው የተጠቀመበት ፣ ከዛ ያገኛቸውን ሁለት ኳሶች መስጠት ችሏል ፣ በተመሳሳይ ለናትናኤልም እንደዚሁ የመጨረሻ ኳስ መስጠት ችሎ ነበር ተሳክቶለታል ማለት እችላለሁ። በሌላ የጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ ጥሩ እገዛ ነበረው ፣ ከሁሉም በላይ ግን የጌታነህ ወደ ጎል መቅረብ ግን የበለጠ ቡድኑን የሚያነሳሳ ነው ፣ እንደዚህ አይነት ነገር መምጣቱ አይቀርም ጊዜ ፈጅቶብናል በዕርግጥ ግን አቅም ያላቸውም ተጫዋቾች ነው ያሉን ሽመክትም ከዚህ በፊት በትልቅ ደረጃ ሲጫወት የነበረ ልጅ ነው አሁንም ከዛው አቋሙ ጋር እንዳለ ነው የሚሰማን ለጎሎቹ መገኘት ግን ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው።”

አሰልጣኝ አስራት አባተ – ድሬዳዋ ከተማ

በመከላከሉ ጥሩ ሆነው በማጥቃቱ ተዳክመው መቅረባቸው አቻ ውጤት ከመፈለግ አኳያ የመጣ ይሆን…

“የተጋጣሚ ቡድን በልምድም ባለው ኳሊቲም የተሻለ አቅም እንዳለው እናውቃለን ፣ ሆኖም ሚዛናዊ የሆነ አጨዋወትን ለመጫወት ነው ይዘን የገባነው ፣ የተደራጀን ሆነን ለመጫወት ሞክረናል ግን ከዕረፍት በፊት ወደ ፊት መሄድ አልቻልንም ያንን የመለወጥ ዕሳቤ ይዘን ነው ከዕረፍት በኋላ የገባነው በተወሰነ መልኩም በአጨዋወታችን ትንሽ ለውጥ ነበረን ፣ በተደጋጋሚ በሰራንበት ፣ በፈራነው ሁኔታ ላይ ተደጋጋሚ የቅጣት ምት ዕድሎችን ተጋጣሚ ቡድን አግኘቶ ነበር እና ያንን ዕድል እስኪያገኝ ድረስ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረን ነበር ከጎሉ በኋላ ግን በተወሰነ መልኩ ክፍተት ነበረብን።”

የቻርለስ ሙሴጌ በተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጥ…

“ቻርለስ ሙሴጌ እንግዲህ ሰሞኑን በጉዳት ላይ ነው ያለው የመጫወት ፊትነሱም ጥሩ አይደለም ፣ እንደዚሁም ጉዳቱም አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለም ያለው ጉዳት ላይ ነው። ኤፍሬምም የጨዋታ ፊትነሱ ጥሩ ላይ አይደለም እንዲሁም ተመስገንም በወጥ ደረጃ ልንጫወት የምንችላቸውን ልጆች አላገኘንም። የቻርለስ ግን በዛሬው ጨዋታ ላይ የጉዳቱ መጠን ከፍተኛም ስለነበር ሊያጫውተው ስላልቻለ ነው።”

ቡድኑ ሊሻሻል ያልቻለበት ምክንያት…

“ከዚህ በፊት የጎል ዕድሎችን እንፈጥር እና በቀላሉ ነው ጎሎችን የምናመክነው ፣ ተጋጣሚያችን በየትኛውም መልኩ ቢደራጅ እኛ ጎል የመፍጠር ችግር የለብንም ፣ የሚቆጠሩብን ጎሎች በቀላሉ ነው የሚገቡብን ዛሬም እንዳየህው ቅጣት ምቱም የገባብን በቀላሉ ነው ሁለተኛውም ኳስ ኮንሰንትሬት ባለማድረግ በቀላሉ ነው ዕድሎችን አሳልፈን እየሰጠን ያለነው ያ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎናል ፣ እኛም አንዳንድ ማሻሻል ያለብንን ነገሮች እያሻሻልን አልመሰለኝም።”

የቡድኑ ውጤት ማጣት አሳሳቢ ነው ማለት ይቻላል…

“መሸነፍ በራሱ ውጤት ማጣት ስለሆነ ያ ሊያሳስብ ይችላል ፣ እንደ ውድድር ከታየ ግን ሁሉም ቡድኖች አሁን እኛ ስምንት ነጥብ ነው ያለን ከእኛ ፊት ያሉት የሦስት ነጥብ ልዩነት ነው ያላቸው ይሄ መስተካከል የሚችል እና አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ብንችል ወደ ፊት የሚያስኬደን ነው ብለን እናስባለን ግን በቀላሉ ጨዋታዎችን መጣል ደግሞ ለቡድናችን አደጋ ነው።”