አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከወሳኙ ፍልሚያ በፊት ሀሳባቸውን ሰጥዋል

ከዓለም ዋንጫው በ180 ደቂቃዎች ርቀት ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር ለሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ ስላደረጉት ዝግጅት የተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ከሰዓት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከናውኗል።

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ቡድኑ ላለፉት 23 ቀናት ሲያደርጉት ስለቆዩት ዝግጅት ገለፃ በጀመረው መግለጫው አሰልጣኙ በተቻላቸው መልኩ ጥሩ ዝግጅት ለማድረግ ቢሞክሩም የዝግጅት ምዕራፉ ግን በፈለጉት መልኩ እንዳልሄደ አልሸሸጉም።

ሀሳባቸውን ሲያስረዱም ለውድድሩ በሚመጥን ደረጃ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ፈልገው የነበረ ቢሆንም ከአንድ የወንድ ቡድን ጋር ብቻ ጨዋታ አድርገው ለጨዋታው መቅረባቸው ቡድናቸውን ለመለየት እንደቸገራቸው እና ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጠቁመዋል።

አያይዘውም በቡድኑ ውስጥ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የዕድሜ እርከን ሀገራቸውን ወክለው ወደ አህጉራዊ ውድድር ለማምራት ጫፍ ደርሰው የቀሩ ልጆች በከፍተኛ ቁጭት እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ ፊቶች ደግሞ ይህን ታሪክ ለመስራት በጥሩ መነሳሳት ላይ እንዳሉ ገልፀዋል።

በመቀጠል በስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አሰልጣኝ ፍሬው ምላሽ ሰጥተዋል ፤ ከተነሱ ሃሳቦች መካከል

ስለውል ማራዘም

“ውሌን ከተጠናቀቀ 16(18) ቀናት አካባቢ ተቆጥረዋል።በግሌ ውልን በተመለከተ ያለውን ነገር መልክ ለማስያዝ ከፌደሬሽኑ ጋር ጥረት አድርግያለሁ በዚህም ለስራ አስፈፃሚው ገለፃ ሰጥቼ እነሱም ተቀብለውኝ ለሁለት ዓመት የሚቆይ አዲስ ውል እንዲሁም የተጣራ 120 ሺህ ብር ሊከፍሉኝ ተስማምተን ወጥቼ ነበር ነገርግን ውሉ ይሰጥሃል ከተባልኩኝ አሁንም ሶስት ወር ተቆጥሯል።ይህ ተቋሙን የሚመለከት ነው እኔ በግሌ ሙያዬን የምሸጥ ሙያተኛ ነኝ በሂደቱ ላይ መታገስ ስላለብኝ እስካሁን ድረስ እየተጠባበኩኝ እገኛለሁ። ሀገሬን የማገለግለው ውል ስላለኝ እና ገንዘብ ስለሚከፈለኝ ብቻ አይደለም። ስለሀገር ዋጋ መክፈል ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቆ ከሚያውቅ ማህበረሰብ ውስጥ እንደመገኘቴ ለ180 ደቂቃ ውድድር ውል አልተሰጠኝም ብዬ የራሴን ጥቅም ከሀገሬ የማስበልጥ ሰው አይደለሁም።ሀገሬን ከእግር ኳስ ሙያዬ ውጭ ባለ መስክ እንኳን በነፃ ለማገልገል ሁሌም ዝግጁ ነኝ።

ቡድኑ ስላደረገው የስነልቦና ዝግጅት

“ከዚህ ቀደም ከጋና ጋር ደርሶን ማለፍ ሳይችል የቀረው ቡድን ብዙም ልምድ የነበረው አልነበረም አሁን ላይ እነዚያ ልጆች በተለያዩ የውድድር መድረኮች በአህጉራዊ ውድድሮች ማጣርያ ላይ የመጫወት ልምድን አግኝተዋል።ለዚህ ውድድር ዝግጅት የተለያዩ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ከሜዳ ላይ ልምምድ ባለፈ የክፍል ውስጥ ትምህርቶችን እየሰጠን እንገኛለን።ከዚህ ባለፈ እጅግ ከፍተኛ ልምድ ያለው ሳዳት ጀማል አብሮኝ ነው ያለው እሱም ካለው የካበተ ልምድ ልጆቹን እያካፈለ እና እያገዘኝ ይገኛል። በዚህ መነሻነት ከቀደመው አንፃር ቡድኑ 100% በስነልቦና ገንብተነዋል ብዬ አስባለሁ።”

ስላልተሳኩት ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄዎች

“ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ እና ከጨዋታው አስቀድሞ ሞሮኮ ላይ ለ7 ቀናት ዝግጅት ለማድረግ እና የአየር ንብረቱን ልናላመድ የምንችልበትን መንገድ ለመፍጠር ጥያቄ አቅርቤ ነበር።ነገርግን ሰባት ቀን በሚል ያቀረብነው ጥያቄ ከሳይንሱ አንፃር የተሻለው አማራጭ ቢሆንም እንደ ሁለተኛ አማራጭ በቀረበው በሶስት ቀን ተስማትተን በዛ መልኩ የምንጓዝ ይሆናል።ከወዳጅነት ጨዋታ ጋር በተያያዘ ግን ላቀረብኩት ጥያቄ ግን ምላሽ አልተሰጠኝም።

የመልሱ ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚደረግ እየታወቀ በአዲስ አበባ ስታዲየም ልልምድ ስለመስራታቸው

“በሞሮኮ የምናደርገው ጨዋታ በሰው ሰራሽ ሜዳ ሳይሆን በተፈጥሮ ሳር ላይ የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በተሻለ ሳር ላይ ልምምድ ለማድረግ በሚል ምርጫችን አድርገነዋል።”

ተጫዋቾቹ ውስጥ አሁን ላይ ስላለው ስሜት

“በመከባበር ላይ የተመሰረተ ፣ ጠንካራ የቡድን መንፈስ እንዲሁም ከፍ ያለ የማሸነፍ ስሜት የተገነባ እና ከፍ ያለ የሀገር ፍቅር ስሜት ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው።”