ኢትዮጵያ ቡና ከዩጋንዳዊው አጥቂ ጋር ተለያይቷል

ኢትዮጵያ ቡናን በሦስት ዓመት ውል ተቀላቅሎ የነበረው ዩጋንዳዊ አጥቂ ከክለቡ ጋር ስለ መለያየቱ ታዋቂው የሀገሪቱ ድረገፅ አስነብቧል።

በ2016 የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ቡናን ለማገልገል በሦስት ዓመት ውል በተሰናባቹ አሰልጣኝ ኒኮላ ካባዞቪች አማካኝነት ፈርሞ የነበረው ዩጋንዳዊው አጥቂ ዴሪክ ካኮዛ ቀሪ ውል ከክለቡ ጋር እየቀረው ከአራት ወራት ቆይታ መልስ ኮንትራቱ በስምምነት መፍረሱን ታውቂው የሀገሩ ድረገፅ ፑልሴ ስፖርትስ ዩጋንዳ አስነብቧል።

የግብፁን ክለብ ኤንፒፒአይን ለቆ ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀል ከሀገራችን እግር ኳስ ጋር መተዋወቅ ችሎ የነበረው ተጫዋቹ በክለቡ ቆይታው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አንድ ጎል በፕሪምየር ሊጉ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ደግሞ ቡድኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ1 ሲረታ ብቸኛዋን ጎል ማስቆጠሩም ይታወሳል።