ጥንዶች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በጋራ ሊመሩ ነው

ነገ የሚደረገውን የሊጉን ጨዋታ የትዳር አጋሮቹ በጋራ በመሆን ሊመሩ እንደሆነ ታውቋል።

በኢትዮጵያውያን ዳኞች ታሪክ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ሁለቱ ጥንዶች በሳምንቱ መጨረሻ የሚካሄደውን እና ኢትዮጵያ ቡናን ከ ወልቂጤ ከተማ የሚያገናኘውን ጨዋታ እንዲመሩ መመደባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ጥንዶቹ ኢንተርናሽናል አርቢቴር አሸብር ሰቦቃ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ ዘውዱ ሲባሉ በትዳር ከተጣመሩ ዓመታት ያስቆጠሩና በትዳር ህይወታቸውም ማርያማዊት የተሰኘች የሦስት ዓመት ሴት ልጅ ያፈሩ ናቸው።

ኢንተርናሽናል አርቢቴር አሸብር ሰቦቃ በዳኝነት ህይወቱ በርከት ያሉ የሊግ ጨዋታዎች በመዳኘቱ ሲታወቅ ኢንተርናሽናል ባጅ ካገኘ ሦስት አመታት አስቆጥሯል። የትዳር አጋሩ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ ዘውዱ በተመሳሳይ ወደ ዳኝነቱ ሙያ ከገባች ዓመታትን ስታስቆጥር በኢንተርናሽናል ዳኝነት ያለማቋረጥ ተከታታይ ለአስር ዓመታት የሰራች ሲሆን በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለት ጊዜ ምስጉን ረዳት ዳኛ በመመባል መመረጥ ችላለች። ከዚህ ቀደም ሣራ ሰዒድ ፣ ሰርካለም ከበደ ፣ ወይንሸት አበራ የመሳሰሉ ረዳት ዳኞች የመሩበት የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ ወጋየሁ ዘውዱም የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዋን በትናትናው ዕለት በአዳማ እና ሀዋሳ መካከል በተደረገው ጨዋታ ላይ መምራቷ ይታወሳል።

 

ከዚህ ቀደም አሁን በኮሚሽነርነት እያገለገሉ የሚገኙት ተስፋዬ ኦሜጋ እና ሣራ ሰዒድ ሁለቱም በረዳት ዳኝነት በጋራ በመሆን የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን የዳኙ ሲሆን ከዓመታት በኋላ ኢንተርናሽናሎቹ ዳኞች ዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ እና ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኛ ወጋየሁ ዘውዱ የነገውን ጨዋታ የሚመሩ ይሆናል።

መሰል ታሪኮች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም እግር ኳስም ያልተለመዱ ሲሆን በዳኝነት ሙያ ትዳር የመሰረቱ በርከቶች ቢሆኑም እንደ ፖሊሾቹ ዳንኤል ስቴፋንስኪ እና ካሮሊና ስቴፋንስኪ በጋራ የዋና ሊግ ጨዋታ የመሩ ብዙም ባይሆኑ እንዳሉ ግን ታሪክ ያስረዳል።