አፍሪካ ዋንጫ | ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን በዛሬ እና ነገ ጨዋታዎች ግልጋሎት ይሰጣሉ

የጥሎ ማለፉ የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ኢንስትራክተር አብርሃም ሲመደብ የነገ ጨዋታ ላይ ደግሞ አልቢትር ባምላክ ተሰይሟል።

34ኛው አፍሪካ ዋንጫ ሳቢ ፉክክር በማሳየት የምድብ ጨዋታዎቹን ካገባደደ በኋላ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን ከዛሬ ጀምሮ ማከናወን ይጀምራል። በዚህ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የመጀመሪያ መርሐ-ግብር አንጎላ እና ናሚቢያ የሚያደርጉት ፍልሚያ ላይ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከኬኒያዊው ሚሼል አሜንጋ ጋር በመሆን የቴክኒክ ጥናት እንዲያደርጉ መመደባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ውድድሩም ነገ ቀጥሎ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጊኒ የሚያደርጉትን የምሽት 2 ሰዓት ጨዋታ ላይ ደግሞ የሀገራችን አልቢትር ባምላክ ተሰማ መመደቡን አውቀናል። ይህንን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ሶማሊያዊው ኦማር አብዱልካድር አርታን ከሁለት ኬኒያዊ ረዳቶቹ ጋር በመሆን የሚመራው ሲሆን በውድድሩ የሀገራችን ብቸኛ አልቢትር የሆነው ባምላክ ተሰማ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ግልጋሎት እንደሚሰጥ ተመላክቷል።