ሪፖርት | ነብሮቹ የድል ረሃባቸውን አስታግሰዋል

ሀድያ ሆሳዕና በዳዋ ሆቴሳ ብቸኛ ጎል ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ባህርዳር ከተማን 1ለ0 በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።

ሀድያ ሆሳዕናዎች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ጎል ከፈፀሙበት ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ግርማ በቀለ ፣ ዳግም ንጉሴ እና ተመስገን ብርሀኑን አስወጥተው በምትካቸው ሔኖክ አርፊጮ ፣ ቃለአብ ውብሸት እና ስንታየሁ ዋለጪን የተኩ ሲሆን በአንፃሩ በአዳማ ከተማ ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት ባህርዳሮች በበኩላቸው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ፍፁም ፍትህአለሙን ከቅጣት በተመለሱት ፍሬዘር ካሳ እና አለልኝ አዘነ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጨዋታውን የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ገና በማለዳው ነበር መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ያስቆጠሩት ፤ 5ኛው ደቂቃ ላይ ሠመረ ሀፍታይ ተረጋግቶ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ዳዋ ሆቴሳ በቀላሉ አላዛር መረብ ላይ አሳርፏት ቡድኑን መሪ አድርጓል።

በጨዋታው በጊዜ ግብ ለማስተናድ የተገደዱት ባህርዳር ከተማዎች በተቆጠረባቸው ግብ ሳይረበሹ በተረጋጋ ሁናቴ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ቢችሉም የተደራጀውን የሀዲያ ሆሳዕናን የመከላከል መዋቅር ግን ለማስከፈት ተቸግረው ተስተውሏል።

የሀድያን የኋላ ክፍል ለመስበር በመቸገራቸው መነሻነት በ23ኛው ደቂቃ አለልኝ አዘነ ከርቀት ካደረጋት እና ታፔ አልዛየር በቀላሉ ካዳነበት ኳስ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራን በአጋማሹ ለማድረግ ተቸግረው ተስተውሏል። በአንፃሩ ለተጋጣሚያቸው ኳሱን በመፍቀድ ኳስን በሚነጥቁበት ወቅት ፈጠን ባሉ ሽግግሮች ወደ ቀኝ በማጋደል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከባህርዳር በተሻለ አስፈሪ የማጥቃት ሂደት ነበራቸው።

በ23ኛው ደቂቃ የባህር ዳር ከተማው የመስመር ተከላካይ ፍራኦል መንግስቱ ባጋጠመው በጉዳት በፍፁም ፍትህዓለው ለመተካት የተገደዱ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ30ኛው ደቂቃ ከያሬድ ባየህ ስህተት የተገኘችን ኳስ ሰመረ ከአላዛር ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ መሪነታቸውን ሊያሳድጉበት የሚችሉበት አጋጣሚ ነበረች።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ጉዳት ባስተናገዱ ተጫዋቾቻቸው ምትክ ለውጥን በማድረግ የጀመሩ ሲሆን ባህርዳሮች ፍፁም ጥላሁንን በአምሳሉ ሳህለ እንዲሁም ሀድያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ሠመረ ሀፍታይን በተመስገን ብርሀኑ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል።

ሀዲያዎች በአጋማሹ በመጠኑ አፈግፍገው ይጫወቱ እንጂ ተመስገን ብርሃኑ ወደ ሜዳ መግባቱን ተከትሎ የተጫዋቹን ፍጥነት በመጠቀም ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋለ ቢሆንም ባህርዳር ከተማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ይበልጥ ሲታትሩ ያስተዋልንበት አጋማሽ ቢሆንም ባህር ዳሮች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የሆሳዕናን የመከላከል መዋቅር ለማስከፈት ግን ሳይቻላቸው ቀርተዋል።

ከጨዋታው በኋላ የባህርዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጠንካራ ጨዋታ እንደነበር ጠቅሰው በጊዜ ያስተናገዱት ጎል ጫና እንደፈጠረባቸው ጠቁመው ወደ ጎል ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም በስሜት ውስጥ ስለነበሩ ግብ ማስቆጠር አለመቻላቸውን ገልፀዋል።በአንፃሩ የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ በኩላቸው ጨዋታው ከባድ መሆኑን ገልፀው አየሩም አስቸጋሪ እንደነበር እና ተጋጣሚያቸው ከተከታታይ ሽንፈት በመምጣቱ ጫናን መፍጠሩን ገልፀዋል።