ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አዲስ አሰልጣኝ አግኝቷል

በሴቶች እግር ኳስ ላይ ጠንካራ ስራዎችን በመስራት የሚታወቀው አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ለአራት ተከታታይ ዓመታት ካሰለጠነው ከአሰልጣኝ ፍሬው ሀይለገብርኤል ጋር ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ መለያየቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በያዝነው ወር የካቲት 29 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በጋና አክራ ሲደረግ የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ላይ የሚሳተፍ ሲሆን ይህን ብሔራዊ ቡድን እንዲመራ ደግሞ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ላይ አበርክቶው ከፍ ያለውን አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ (ወፍዬ) ስለመሾሙ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።

በርከት ያሉ ዓመታትን ከወንዶች ጎን ለጎን የሴት ቡድንን በፕሮጀክት በማሰልጠን በመቀጠል ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሲቋቋም ሀዋሳ ከተማን ለስምንት ዓመታት በመያዝ ክለቡን በሊጉ በተከታታይ ዓመታት ሦስተኛ እንዲወጣ በማድረግ እንዳሁም ደግሞ የጥሎ ማለፍ እና የዙር ውድድሮችን እንዲያሸንፍ አሰልጣኙ በክለቡ ቆይታቸው ያገኛቸው ክብሮች ናቸው። ሎዛ አበራን ጨምሮ በርካታ ሴት ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያበረከተው እና ያለፉትን ሦስት ዓመታት የአርባምንጭ የሴቶች ክለብን ያሰለጠነው ዮሴፍ ገብረወልድ አዲሱ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኗል።