ጎፈሬ እና ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ተጣምረዋል

ግዙፉ የሀገር በቀል ስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ለሶስት ዓመታት በሚቆይ የውል ስምምነት ብራድ አምባሳደሩ በማድረግ መሰየሙን ዛሬ ከሰዓት በነበረ ሁነት አስተዋውቋል።

ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው የተቋሙ አዲሱ ሾው-ሩም በነበረው ሁነት ሁለቱ አካላት በጋራ በመሆን መግለጫ የሰጡ ሲሆን ፤ በቅድሚያ ስለስምምነቱ ማብራሪያ የሰጡት የጎፈሬ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሳሙኤል መኮንን ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸው የዛሬው ስምምነት ለጎፈሬ ምርቶችን ከማስተዋወቅ በዘለለ ትልቅ ትርጉም ያለው ስለመሆኑ የገለፁ ሲሆን በዚህም የዛሬው የስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት የታዳጊዎች ስልጠና ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ከሌሎች የብራንድ አምባሳደርነት ስምምነቶች የተለየ እንደሚያደርገው አንስተዋል።

አቶ ሳሙኤል አያይዘውም ጎፈሬ የታዳጊዎች ስልጠና ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ሲሰራ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ አንስተው ከዚህ ቀደም ከሁለት ተቋማት ጋር በአጋርነት ድጋፎችን ስለማድረጋቸው ገልፀው ይህ የዛሬው ስምምነትም ለሶስት ዓመታት የሚቆይ በየዓመቱ መጠኑን እየጨመረ የሚሄድ የድጋፍ ማዕቀፍ እንደሆነ እና በቀጣይም ይህ ስምምነት ወደ ፋውንዴሽን የማደግ ትልም ያለው ስምምነት ነው ሲሉም ገልፀዋል።

አክለውም ይህ ስምምነት ይፋ ለማድረግ የተቃደው ከወራት በፊት ቢሆንም ኢንስትራክተር አብርሃም ከነበራቸው የተለያዩ አህጉራዊ ተልዕኮዎች መነሻነት ጊዜው እንደገፋ ገልፀው ምንም እንኳን ስምምነቱ ዛሬ በይፋ ቢበሰርም ሁለቱ አካላት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት ከጀመሩ ሰንበትበት ማለታቸው ተናግረዋል።

በማስከተል መድረኩን የተረከቡት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ሲሆኑ በመግቢያቸውም ስምምነቱ ከምርትን ማስተዋወቅ የዘለለ አላማን ያነገበ በመሆኑ በደስታ ስለመቀበላቸው አንስተው ስምምነቱ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ፣ በሙያቸው ታዳጊዎች ላይ የሚሰሩ አሰልጣኞችን በቀጥታ ሊያግዙበት የሚችሉበት እንዲሁም ሌሎች ሙያተኞች በመሰል እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማነሳሳት በማለም ጥያቄውን ስለመቀበላቸው አብራርተዋል።

በማስከተል በሁለቱ አካላት መካከል ስምምነቱን የሚያፀና ይፋዊ የፊርማ ስነ-ስርዓት የተከናወነ ሲሆን አስከትሎም በስፍራው ከታደሙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በሁለቱ አካላት በኩል ምላሽ የተሰጠበት ነበር።

ኢንስትራክተር አብርሃም ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ በስምምነቱ መሰረት ድጋፎቹ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የታዳጊዎች የፓይለት ፕሮጀክት በሚደርስባቸው አካባቢዎች በሙሉ በሁለቱም ፆታዎች ተደራሽ ለማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነ አንስተው የድጋፍ ማዕቀፉ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር በመናበብ የሚሰራ መሆኑንም እንዲሁ በምላሻቸው ውስጥ አንስተዋል።

አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው ተቋማቸውን በሚመለከት ለተነሱ ጥያቄዎች ሲመልሱ ኢንስትራክተር አብርሃምን ለዚህ ዓላማ ስለመረጡበት ምክንያት ሲያስረዱ ኢንስትራክተር አብረሃም በግሉ ከተቋማት በላይ አበርክቶ ያለው ራሱን የቻለ ብራንድ ነው ሲሉ የገለፆት ሲሆን ረዘም ባለ ሂደት በጥናት ላይ ተመርኩዘው ምርጫቸው እንዳደረጉት ሲገልፁ ስምምነቱ የአብርሃምን ሌጋሲ ለማስቀጠል በግሉ ለታዳጊዎች ለመደገፍ ያለውን ውጥን ተቋማዊ ይዘት የሰጠ ስምምነት ነው ያሉ ሲሆን በዚህም የመርሃግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።