ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ተጫዋቾችን አሳድጓል

ቡናማዎቹ ከ20 ዓመት በታች ቡድናቸው ሦስት ተጫዋቾችን ማሳደጋቸውን ይፋ አድርገዋል።

በአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የሚመራው እና በአሰልጣኙ ከተያዘም በኋላ በእጅጉ መሻሻሎች የሚታዩበት ኢትዮጵያ ቡና የፕሪምየር ሊጉን የሁለተኛ ዙር የውድድር ጉዞ የፊታችን ዕሁድ ከሲዳማ ቡና ጋር በማድረግ ይጀምራል። በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን በቡድኑ ውስጥ ይዞ የሚገኘው ክለቡ ሦስት ታዳጊ ወጣቶችን ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ማሳደጉን እና ለቀጣዮቹም አምስት ዓመታት ስለ ማስፈረሙ ይፋ አድርጓል።

የአንድ ወር የሙከራ ጊዜን ተሰጥቷቸው የነበሩት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከዛም በቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ቆይታ የነበረው የተከላካይ አማካዩ ሚኪያስ ፀጋዬ ፣ በሲዳማ ቡና በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ የነበረው የአጥቂ አማካዩ ናትናኤል ፍሬው እና የግራ መስመር ተከላካዩ ናሆም ሲሳይ ናቸው ወደ ዋናው ቡድን ያደጉት።