ድሬዳዋ ከተማ አጥቂ አስፈርሟል

የምስራቁ ክለብ የመስመር ተጫዋች ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በአሠልጣኝ ሽመልስ አበበ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ16 የሊጉ ጨዋታዎች 22 ነጥቦችን በመያዝ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን በሜዳቸው የሚደረገውን የሁለተኛውን ዙር የመክፈቻ ጨዋታም በድል ጀምረዋል። ክለቡ በዙሩ የበለጠ ተጠናክሮ ለመቅረብ ያለፍትን ቀናት ጥረት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን ውጥኑ ሰምሮም አጥቂ ማስፈረሙ ተረጋግጧል።

ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች አሜ መሐመድ ነው። የቀድሞ የጅማ አባቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወልቂጤ ከተማ እና አዳማ ከተማ ተጫዋች የሆነው አሜ በዘንድሮ ዓመት መባቻ ወልቂጤ ከተማን ተቀላቅሎ የነበረ ቢሆንም ከክለቡ ጋር ከግማሽ ዓመት በላይ መዝለቅ ሳይችል ወደ ምስራቁ ክለብ አምርቷል።