ሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2008
የባዬ ገዛኸኝ የ6 ወር እገዳ ፀናበት
በ15ኛው ሳምንት መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ባሳየው ያለልተገባ ባህርይ በቀይ ካርድ ተወግዶ የነበረው ባዬ ገዛኸኝ በፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ የ6 ወራት እገዳ ተላልፎበታል፡፡
መከላከያ የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ጠይቆ የነበረ ሲሆን ይግባኙ እስኪታይ ድረስም አጥቂው የቀይ ካርድ ቅጣቱን ጨርሶ እንዲጫወት ተፈቅዶለት ከሲዳማ ቡና ጋር በተደረገው ጨዋታ ተሰልፎ ግብ ማስቆጠር ችሎ ነበር፡፡
አሁን ደግሞ የዲሲፕሊን ኮሚቴው በውሳኔው በመፅናት ባዬ ገዛኸኝን ለስድስት ወር እንዳይጫወት አግዶታል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት የቡና አመራሮች ለሰኔ 13 ተቀጥረዋል
በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ፕሬዝዳንት እና የደጋፊ ማህበር አመራሮች ክስ ተመስርቶባቸው ዛሬ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ መደበኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ቀርበዋል፡፡
በችሎቱ አቃቤ ህግ ምርመራውን ለማጠናከር ይረዳው ዘንድ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ተጨማሪ ሰባት ቀን (ለሰኔ 13) ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
” ካሳለፍነው ደካማ ጊዜ ትምህርት ወስደናል” አቶ ሚካኤል አምደመስቀል
ደደቢት በውጤት ማጣት ከአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ጋር ከተለያየ በኋላ በጊዜያዊነት ቡድኑን በተረከቡት ኤልያስ ኢብራሂም እየተመራ ከዳሽን ቢራ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በድል ተወጥቷል፡፡
የክለቡ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል አምደመስቀልም ክለቡ በትክክለኛው መንገድ መጓዝ እንደጀመረ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
” አሁን ሙሉ ለሙሉ በመጀመርያው ዙር የነበረን ጥንካሬ መመለስ ላይ ነው ። ያሳለፍነው ደካማ ጊዜ ጥሩ ትምህርት ሰጥቶን አልፏል፡፡ ከዳሽን ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይተናል፡፡ በቀሪው የሊጉ ጨዋታ ላይ ጥሩ ደረጃ ላይ ሆነን መጨረስ እንፈልጋለን ፣ ለቀጣይ አመት ተጠናክረን ለመቅረብ በሚያስፈልጉን ነገሮች ላይም እንሰራለን ” ብለዋል፡፡
እሁድ ሰኔ 5 ቀን 2008
02:00 – ወንድሜነህ ዘሪሁን በአዳማ ታገዷል
የአዳማ ከተማው አማካይ ወንድሜነህ ዘሪሁን በክለቡ መታገዱ ታውቋል፡፡
ክለቡ አማካዩን ለማገድ ከውሳኔ ላይ የደረሰው በዲሲፕሊን ጉዳይ ሲሆን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት እንደነበር ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
01:40 – የአክሱም የደጋፊዎች ግጭት
የስታድየም ረብሻዎች በመላ ሃገሪቱ እየተዛመቱ ይገኛል፡፡ ትላንት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አክሱም ከተማ ከ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት ጨዋታ መጨረሻም አላማረም፡፡
እንግዳው ወልዋሎ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ባስቆጠረው ግብ ጨዋታው በወልዋሎ 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኀላ በሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተከስቷል፡፡ የዳኛ ውሳኔ እና በደጋፊዎች መካከል የነበረውን መበሻሸቅ ተከትሎ በተጀመረው ግጭት በርካታ ደጋፊዎች እና የፀጥታ ሀይሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ግጭቱ እስከ ምሽት በመዝለቁም ተጫዋቾች ሜዳውን ለመልቀቅ እስከ ምሽት 3:30 ድረስ ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግርኳስ አልፎ አልፎ ሲከሰት የነበረው የደጋፊዎች ረብሻ አሁን አሁን እየተደጋገመ እና የአስከፊነቱ መጠን በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል፡፡
01:30 – ዛሬ የተካሄዱ ጨዋታዎች ውጤቶች
ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መካከለኛ-ሰሜን ዞን
ልደታ ክ/ከተማ 1-3 ዳሽን ቢራ
ኢትዮጵያ ቡና 1-3 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ መካከለኛ ዞን
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 አፍሮ ፅዮን
01:15 – የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በስብሰባዎች ተጠምዷል
ባሳለፍነው አርብ በኢትዮዽያ ቡና እና በሀዋሳ ከተማ መካከል በተካሄደው ጨዋታ ላይ በተፈጠረውን የሰው ጉዳትና የንብረት ውድመት አስከትሎ ሊወሰድ ስለሚገባው ውሳኔ ከስፖርት ኮሚሽን ፣ ከሊግ ኮሚቴ ፣ ከዲሲፒሊን ኮሚቴ አና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ረጅም ሰአት የፈጀ ስብሰባ እያደረገ ይገኛል፡፡
ነገ የዲሲፒሊን ኮሚቴ በሚያደርገው ስብሰባ ደግሞ በሁለት መሰረታዊ ነገሮች ላይ እንደሚወያይ ይጠበቃል፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ ጨዋታው ይቀጥል አይቀጥል የሚለው ሲሆን ለደረሰው የአካል ጉዳት የንብረት ውድመት መተዳደርያ ደንቡን መሰረት ያደረገ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
01:30 – በፕሪሚየር ሊጉ ነገ አንድ ጨዋታ ይደረጋል
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ነገ በወላይታ ድቻ እና መከላከያ መካከል በሚደረግ ጨዋታ ይጀምራል፡፡
* ሶከር ኢትዮጵያ ጨዋታውን ከቦዲቲ በቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት ወደ እናንተ ታደርሳለች፡፡
01:00 – መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ነገ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይችላሉ
የአርቡን የስታድየም ረብሻ ተከትሎ የአአ ፖሊስ ኮሚሽን የክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞን ጨምሮ የቡድን መሪውን እና የደጋፊ ማህበሩ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወቃል፡፡
ኮሚሽኑ ለረብሻው ተጠያቂ ናቸው በሚል ክስ የመሰረተባቸው ሲሆን ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና የአአ ፖሊስ ኮሚሽን የስታድየሙ ሰራተኞች በተፈጠረው ጉዳይ ላይ ቃላቸውን እንዲሰጡ ማድረጉ ታውቋል፡፡
12:50 – U20 : የኢትዮጵያ እና ጋና ጨዋታ ለነገ ተላለፈ
በአፍሪካ ከ20 አመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ጋና ከ ኢትዮጵያ 12:00 ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በኬፕ ኮስት ከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያም ጨዋታው መካሄድ እንደሌለባት በመግለጿ ጨዋታው ለነ ተዘዋውሯል፡፡
በዚህም ምክንያት ጨዋታው ነገ በተመሳሳይ ሰአት የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በከተማው የጣለው ዝናብ ነገም የሚቀጥል ከሆነም ወየ ሌላ ከተማ ሊዞር ይችላል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ ጨዋታውን አድርጎ ነገ ወደ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ቢጠበቅም በ1 ቀን የሚራዘም በመሆኑ ሀሙስ የሚደረጉ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ላይ ሽግሽግ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
05:00 – የኢትዮጰያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰላለፍ
ከ20 አመት በታች ቡድኑ አመሻሽ 12:00 ላይ ጋናን ይገጥማል፡፡ የቡድኑ የመጀመርያ 11 ተሰላፊዎችም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1 ተክለማርያም ሻንቆ
8 እንየው ካሳሁን – 2 ሃይደር ሙስጠፋ – 6 ተስፋዬ ሽብሩ – 7 ደስታ ደሙ
16 ዘላለም ኢሳያስ – 13 ዘሪሁን ብርሃኑ (አምበል)
17 ዳዊት ማሞ – 11 ዳዊት ተፈራ – 15 ሚካኤል ለማ
9 አሜ መሃመድ
ቅዳሜ ሰኔ 4 ቀን 2008
የወልድያ እና አማራ ውሃ ስራ ጨዋታ መቋረጥ ጉዳይ
ዛሬ መልካ ቆሌ ላይ በወልድያ እና አማራ ውሃ ስራ መካከል ሲካሄድ የነበረው ጨዋታ ሁለተኛው አጋማሽ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡
ጨዋታው እንዲቋረጥ መንስኤ የሆነው አማራ ውሃ ስራ ጨዋታውን ቢጨርሱ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን በመግለፃቸው መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
አማራ ውሃ ስራዎች ጨዋታውን ለመጫወት አስተማማኝ እና ለደህንነታችን በቂ ዋስትና ካልተሰጠን ለመቀጠል እንቸገራለን በማለት ጨዋታውን መቀጠል እንደማይችሉ አሳውቀው መውጣታቸውን የገለፁ ሲሆን ወልድያዎች ደግሞ በተረጋጋ ነገር ውስጥ እረፍት ላይ አንጫወትም በማለታቸው ተቋርጧል ይላሉ፡፡
በጉዳዩ ዙርያ የከፍተኛ ሊጉ ሀላፊ አቶ ጌታቸውን ማብራርያ ብንጠይቅም የኮምሽነሩና የዳኞች ሪፖርት እስካልደረሳቸው ድረስ ይህ ነው ማለት እንደማይችሉ ጠቅሰዋል፡፡
አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ እና ረዳታቸው ያሉበት አልታወቀም
የዳሽን ቢራ ዋና አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ እና ረዳታቸው ከደደቢት ሽንፈት በኋላ የገቡበት አልታወቀም፡፡ በዛሬው እለትም ዳሽን ቢራ በቡድን መሪውና በአስራት መገርሳ አማካኝነት ልምምዱን በአዳማ አበበ በቂላ ሰርቷል፡፡
የዳሽን የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ ተገኝ እቁባይ ቡድኑን በጊዜያዊነት ሊረከቡ እንደሚችሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እና ሲዳማ ቡና ተለያይተዋል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በጊዜያዊነት የተረከቡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከሲዳማ ቡና ጋር መለያየታቸው ታውቋል፡፡
የአሰልጣኝ ዘላለም ረዳት የነበሩት አለማየሁ አባይነህ በጊዜያዊነት የቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑ ሲሆን ትላንት ሲዳማ ቡናን እየመሩ ኤሌከትሪክን 5-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ጋናን የሚገጥመው የ18 ተጫዋቾች ስብስብ ታውቋል
የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ነገ ጋናን ይገጥማል፡፡ አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሃንስም ጋናን የሚገጥመው የ18 ተጫዋቾች ስብስብ ይፋ አድርገዋል፡፡
አጥቂው ሱራፌል አወል በልምምድ ላይ በደረሰበት ጉዳት ከ18 ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን አልቻለም፡፡
ስብስቡ ይህንን ይመስላል፡-
ምንተስኖት የግሌ ፣ ሚካኤል ለማ ፣ ተክለማርያም ሻንቆ ፣ ተስፋዬ ሽብሩ ፣ ዳዊት ተፈራ ፣ ሃይደር ሙስጠፋ ፣ አሚ መሐመድ ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ደስታ ደሙ ፣ ዘላለም ኢሳያስ ፣ ዳዊት ማሞ ፣ ጊት ጋትኮት ፣ ኪዳኔ አሰፋ ፣ ሃብታሙ ገዛኸኝ ፣ ዘሪሁን ብርሃኑ ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ ፣ አቡበከር ሳኒ ፣ ጀሚል ያዕቆብ
የአአ ፖሊስ ኮሚሽን ማሳሰቢያ ሰጥቷል
ትላንት በኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት መቋረጡን ተከትሎ የአአ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ኮሚሽኑ በመግለጫው በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ አያይዞ አጥፊዎችን ለይቶ ለመቅጣት ምርመራ እያደረገ መሆኑንና እርምጃም እንደሚወስድ ጠቅሷል፡፡ ችግሩ እንዳይደገም ከሚመለከተው አካል ጋር እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተካሄደ አንድ ጨዋታ ኤሌክትሪክ እቴጌን 1-0 አሸንፏል፡፡
የአአ ተስፋ ሊግ የዛሬ ውጤት
ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 ኢትዮጵያ ቡና
የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ውጤቶች
ደደቢት 3-1 ኢ/ወ/ስ አካዳሚ
ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-2 አአ ከተማ