የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መቻል እና ሲዳማ ቡና ድል አስመዝግበዋል

የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ሲዳማ ቡና በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፏል።

በፕሮግራም መደራረብ ምክንያት የሰዓት ለውጥ ተደርጎበት ቀን 8:00 ሰዓት ላይ በተደረገ መርሃ ግብ ሀምበርቾ ከተማ ከመቻል ተገናኝቶ ሀምበርቾ ከሁለት ተከታታይ ድል በኋላ ነጥብ ሲጥል መቻል ከእረፍት በፊት እና ከእረፍት መልስ ባስቆጠሩት ግቦች ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።


ጨዋታውን ብልጫ በመውሰድ የጀመሩት መቻሎች ጨዋታው በተጀመረ በ4ኛው ደቂቃ ቤተልሔም ታምሩ ከፍፁም ቅጣት ምት መምቻ ውጪ ሆና አክርራ መጥታ ባስቆጠረችው ግሩም ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ምንም እንኳን ግብ ቢያስተናግዱም ሀምበርቾዎች በአንፃሩ ኳስን ተቆጣጥረው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ለመመለከት ተችሏል።

መቻል ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ መሪነቱን ለማጠናከር ሀምበርቾ ደግሞ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተቆጣጥረው ቶሎ ቶሎ ወደግብ በመድረስ በሚያድርጉት ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ ፉክክር የታየበት አርባ አምስት ነበር።ሆኖም ግን ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የጨዋታ እንቅሰቃሴ ያስመለከቱበት ነበር።መቻሎች በተጋጋሚ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በመድረስ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል።በ69ኛው ደቂቃ ኳስን ይዘው በገቡበት ቅፅበት የሀምበርቾ ከተማ ተከላካዮች ባደረጉት ንክክ ፍፁም ቅጣት ምት ለመቻሎች ተሰጥቷቸው ቤተልሔም ታምሩ ከመረብ ጋር አገናኝታ መሪነታቸው መስፋት ችላለች።

ጨዋታው ሊገባደደ አከባቢ ሀምበርቾ ከተማዎች በሄለን መንግስቱ ላይ የመቻል ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግንተው ወደጨዋታው መመለስ ሚችሉበትን አጋጣሚ ብርሃን ሀይለስላሴ አምክናለች።በዚህም ጨዋታው በመቻል 2ለ0 አሸናፊነት ተገባዷል።

ቀን 10:00 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከይርጋጨፌ ቡና ተገናኝተው ሲዳማ ቡና በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፏል።

በቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የጀመረው ይሄኛው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች መከካል የመከላከል ባህርይ የታየበት ነበር።ሆኖም ግን በ20ኛው ደቂቃ ሲዳማ ቡና ኳስን ይዘው ወደፍፁም ቅጣት ምት መምቻ ክልል በሚገቡበት ሰዓት የይርጋጨፌ ቡና ተከላካዮች በሰሩት በእጅ ንከክ ፍፁም ቅጣት ምት ለሲዳማ ቡና ተሰጥቶ ፍርማዬ ከበደ ከመረብ ጋር አገናኝታ ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጋለች።

ግብ መቆጠሩ ጨዋታው ወደአንድ ጎን እንዲያደላ አድርጓል።በዚህም ሲዳማ ቡና የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችሏል።ሲዳማ  ቡና በመረጋጋት ኳስን ተቆጣጥሮ በነፃነት ሲጫውቱ እና በተደጋጋሚ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በቶሎ ቶሎ ሲደርሱ ለመመለከት ተችሏል።ይርጋጨፌ ቁና በአንፃሩ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል።

በ36ኛው ደቂቃ ማህሌት ምትኩ ርቀት ላይ ሆና አክርራ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥራ ሲዳማ ቡና 2ለዐ እንዲመራ ሆኗል።በዚህ ብቻ ያላበቁት ሲዳማ ቡናዎች በ42ኛው ደቂቃ በድጋሚ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ የይርጋጨፌ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ መስሏቸው በሚዘነጉበት ወቅት ማህሌት ምትኩ ኳሱን አግኝታ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ በቀላሉ ግብ አስቆጥራ የመጀመሪያ አጋማሽ 3ለ0 በሲዳማ ቡና መሪነት ሊጠናቀቅ ተገዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ እምብዛም የግብ ሙከራ ያልታየበት ነበር።ሆኖም ግን ሲዳማ ቡና ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲጥር ተስተውሏል።በ51ኛው ደቂቃ ቤዛዊት ንጉሴ ከመስመር ወደግብ ያሻማችውን ኳስ የይርጋጨፌዋ ተከላካይ መሠረት ምክሬ ለግብ ጠባቂያቸው ለማቃበል ስትሞክር ግብ ጠባቂዋ ቀድማ ኳስን ለመቆጣጠር ወደሌላ አቅጣጫ ሄዳ ስለነበር ኳሱ ከመረብ ጋር ተገናኝቶ ሲዳማ ቡና 4ለዐ እንዲመራ ሆኗል።

4 ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን እንደጨረሱ የገባቸው ሲዳማ ቡናዎች በሰፊ ግብ ልዮነት በመምራታቸው ጠዋታው ግለቱን እያጣ እንዲመጣ ሆኗል።በዚህም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለከት ጨዋታው በሲዳማ ቡና 4ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።