አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የአራት ጨዋታዎች ዕገዳ ተላለፈባቸው

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በሳምንቱ መጨረሻ የተደረጉ ጨዋታዎችን ተንተርሶ በአንድ አሰልጣኝ፣ በሁለት ተጫዋቾች እና በአንድ ክለብ ላይ ቅጣትን አስተላልፏል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታ መቻል በባህርዳር ከተማ 1ለ0 በተረታበት ጨዋታ የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከተጋጣሚያቸው ባህርዳር ከተማ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጋር ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ለጠብ የሚያነሳሳ የስነምግባር ጥሰት ድርጊትን ስለ መፈፀማቸው ሪፖርት በመቅረቡ አሰልጣኙ በዕለቱ ለፈፀሙት ድርጊት አራት ጨዋታዎች እንዲታገዱ እና በተጨማሪም የአምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትን እንዲከፍሉ በአሰልጣኙ ላይ ተወስኖባቸዋል።

በተያያዘ የተጫዋች ቅጣት ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ 1ለ1 ባጠናቀቁት ጨዋታ ከዕረፍት በፊት የወላይታ ድቻው አጥቂ ቢኒያም ፍቅሬ እና የአዳማ ከተማው አማካይ አድናን ረሻድ ሜዳ ላይ ዕርስ በዕርስ በፈጠሩት ፀብ በቀጥታ ቀይ ካርድ በዕለቱ ዋና ዳኛ እያሱ ፈንቴ የተወገዱ ሲሆን ተጫዋቾቹ ለፈፀሙት ድርጊት የሦስት ጨዋታዎች ዕገዳ እና የሦስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እያንዳንዳቸው እንዲከፍሉ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

በክለብ ደረጃ ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ1 በረታበት ጨዋታ የድሬዳዋ ደጋፊዎች ድንጋይ በመወርወራቸው የ25 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት በክለቡ ላይ ተላልፏል።