ሀምበሪቾ ዩጋንዳዊ አጥቂ አስፈርሟል

ተመስገን ዳናን አዲሱ አሰልጣኙ ያደረገው ሀምበሪቾ ዩጋንዳዊ አጥቂ ማስፈረሙን የሀገሪቱ ተነባቢ ድረ-ገፅ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ባደገበት ዓመት በወራጅ ቀጠናው ግርጌ ላይ ተቀምጦ የሚገኘው ሀምበሪቾ ከአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ስንብት በኋላ በረዳት አሰልጣኙ መላኩ ከበደ ሲመራ ረጅሙን የሊግ ጉዞ ካሳለፈ በኋላ በመጨረሻም ከቀናት በፊት አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በሊጉ ለመቆየት በማሰብ መቅጠሩ ይታወሳል።

በክለቡ የሚገኙ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር እንደሌሉ የታወቀ ሲሆን በሌሉ ተጫዋቾች ምትክም የዝውውር ወቅቱን በመጠቀም ዩጋንዳዊውን አጥቂ ካሪም ንዱጉዋን ቡድኑ ማስፈረሙን የሀገሪቱ ታዋቂ ድረ-ገፅ ፑልሴ ስፖርት ዩጋንዳ አስነብቧል።

በዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ በሆኑት ቡል እና ቫይፐርስ የተጫወተው የ31 ዓመቱ አጥቂ ወደ ሀገራችን ሊግ በመምጣት የተመስገን ዳናውን ቡድን መቀላቀሉን ነው ድረ ገፁ ያስነበበው።