ሪፖርት | ማራኪው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹን ባለ ድል አድርጓል

26 የግብ አጋጣሚዎች በተፈጠሩበት ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 3ለ1 ረቷል።

ባህር ዳሮች በመቻል ላይ ካስመዘገቡት ድል የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ በፍፁም ፍትሕአለሙ ፣ ዓባይነህ ፌኖ እና ጉዳት በገጠመው አለልኝ አዘነ ቦታ ፍራኦል መንግሥቱ ፣ በረከት ጥጋቡ እና ሙጂብ ቃሲምን ሲተኩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው በድሬዳዋ ሽንፈት የገጠመው ቡድናቸውን ሳይለውጡ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሩት የሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሜዳ ላይ ከነበሩ የኳስ መንሸራሸሮች በስተቀር አደገኛ ሙከራን ለመመልከት ረጅም ደቂቃን ለመጠበቅ የተገደድንበት ነበር። ኢትዮጵያ ቡና ኳስን በመቆጣጠር ከራስ ሜዳ በምቾት በሚደረጉ ቅብብሎች በይበልጥ የመስፍን ታፈሠን የግራ መስመር በመጠቀም በኋላ ላይም ወደ ግብ በሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም የሚያደርጓቸው የመፍጠሪያ መንገዶች ግን ስኬታማ አላደረጋቸውም። ለተጋጣሚያቸው ነፃነትን ይፍቀዱ እንጂ ኳስን ሲያገኙ ወደ ቸርነት ጉግሳ የግራ የሜዳ ክፍል አዘንብለው ሲጫወቱ አደገኛ መልክ የነበራቸው ባህርዳሮች የቡናን የመከላከል አጥር ለመስበር በድግግሞሽ ፋታ የለሽ ጥረቶችን አድርገው በጨዋታው በመጨረሻም ጥራት ያላትን ሙከራ 23ኛው ደቂቃ ላይ ተመልክተናል።

ቸርነት ከቀኝ ወደ ውስጥ ይዞ ገብቶ ለፍሬው ሲሰጠው አማካዩ ወደ ቀኝ ለነበረው መሳይ አገኘሁ አቀብሎት ገፋ በማድረግ ተከላካዩ በቀጥታ መቶ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ አድኖበታል። ቡናማዎቹ በሂደት ከነበራቸው ግለት ወረድ ማለታቸውን ተከትሎ በተሻለ ይዘት ብልጫን እየያዙ የመጡት የጣና ሞገደቹ 33ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ግብ ወደ ቋታቸው ከተዋል። በፍቃዱ ለአብዱልከሪም የሰጠውን ኳስ በፍጥነት የነጠቀው የአብስራ ተስፋዬ ከቀኝ ወደ ውስጥ በአግባቡ ያቀበለው ኳስ ሙጂብ ቃሲም ወደ ግብነት በመለወጥ በባህርዳር መለያ የጎል አካውንቱን ከፍቷል። ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ የመከላከል መዋቅራቸው ደካማነቱ እየጎላ የሚታይባቸው ቡናማዎቹ 45+2 ላይ ሁለተኛ ጎልን አስተናግደዋል። ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጀ ኳስን ለማቀበል የተሳሳተውን ኳስ ሀብታሙ ታደሠ ነጥቆ በጥሩ የእግር ስራ ከፍሬው ጋር ተቀባብሎ ዳግሞ የደረሰውን ኳስ በቀድሞው ክለቡ መረብ ላይ አሳርፎ አጋማሹ በባህርዳር የ2ለ0 ውጤት ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡና ወንድሜነህ ደረጀ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ ፣ አስራት ቱንጆ እና ብሩክ በየነን አሳርፈው ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ አማኑኤል አድማሱ ፣ ኪያር መሐመድ እና ስንታየሁ ዋለጪን ወደ ሜደ ሲያስገቡ ባህርዳሮች ሙጂብ ቃሲምን በፍፁም ጥላሁን በብቸኝነት ከለወጡ በኋላ ጨዋታው ቀጥሏል። ካደረጓቸው አራት ለውጦች በኋላ ከፍ ባለ ተነሳሽነት በባህርዳር ላይ ጫናን ማሳደር የጀመሩት ቡናማዎቹ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት በተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈፅመዋል። 51ኛው ደቂቃ በፍቃዱ ከማዕዘን አሻምቶ ግብ ጠባቂው ፔፕ ሰይዶ በያዛት አጋጣሚ የጀመረው ሙከራቸው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግብን አስገኝቶላቸዋል። 53ኛው ደቂቃ ኪየር ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ መስፍን በግንባር ገጭቶ ፔፕ ሰይዶ የተፋትን ኳስ አንተነህ ተፈራ ወደ ጎልነት ቀይሮ ጨዋታው 2ለ1 ሆኗል።

የባህርዳርን ያልተረጋጋ የኋላ ክፍል በሚደረጉ የመሐል ለመሐል እና የመስመር አጨዋወት ጫና ውስጥ የከተቱት የአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ልጆች አንነተህ ተፈራ ካመከናት ግልፅ አጋጣሚ መልስ 58ኛ ደቂቃ ላይ ስንታየው ከወልደአማኑኤል ያገኘውን ኳስ መስፍን ታፈሠ ደርሶት ወደ ውጪ ሰዷታል። እንደነበራቸው ብልጫ ተጨማሪ ጎሎችን ከመረብ ለማገናኘት መቻኮሎች የሚታይባቸው ቡናማዎቹ ቀስ በቀስ የሚቋረጡ ኳሶችን በሽግግር ለመጫወት ተጋጣሚያቸው ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ምላሻቸው ደብዛዛ መሆን መቻሉ ተጨማሪ ጎል እንዲቆጠርባቸው አድርጓል። የቸርነት አስፈሪ እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ የጥቃት መነሻን በፍፁም ያደረጉት የጣና ሞገዶቹ 66ኛ ደቂቃ ፍፁም እና ሀብታሙ ነክተዋት ቸርነት ወደ ግብ መቶ በረከት ካዳናት በኋላ 72ኛው ደቂቃ ፍሬው ሠለሞን ወደ ቀኝ ያቀበለውን ችርነት የባህርዳር ሦስተኛ ጎል አድርጓታል።

የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ግቦችን ለማግኘት መታተር ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች 77ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ሞክሮ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት እና 81ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለማየሁ በግል ጥረቱ ከቀኝ ወደ ውስጥ ይዞ የገባውን ኳስ ሞክሮ ፔፔ ሰይዶ በያዘበት አጋጣሚ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ቢጥሩም ጨዋታው በመጨረሻም በባህርዳር ከተማ 3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታዉ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በመጀመሪያው አርባ አምስት ጥሩ አለመሆናቸውን ገልፀው በተጋጣሚያቸው መሻል ሳይሆን በራሳቸው ስህተት ጎል እንዲስተናገዱ ጠቁመው ከዕረፍት በኋላ ግን ብልጫ በመውሰድ በእንቅስቃሴ የተሻልን ብንሆንም አልተሳካም በተጫዋቾቻቸውም ላይ ድካም እንዳለም አስረድተዋል። የባህርዳር ከተማው አቻቸው ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው ቡድኑ ጫና ውስጥ እንደነበር እና በተከታታይ ጨዋታዎች ማገገሙን አውስተው በውጤቱ ይገባል በእንቅስቃሴም የተሻልን ነበርን ካሉ በኋላ አስጨናቂ እና ጠንካራ የሆነውን ኢትዮጵያ ቡናን ተቋቁመው ማሸነፋቸው ደስ እንዳሰኛቸው ጭምር ገልፀዋል።