ድሬዳዋ ከተማ የተላለፈበት ውሳኔ እንዲታገድለት ለፌዴሬሽኑ አቤቱታውን አሰምቷል

የሊጉ አክስዮን ማኅበር የውድድር እና ስነ ሥርዓት ኮሚቴ በድሬዳዋ ከተማ ላይ ያስተላለፈውን የገንዘብ ቅጣትም ሆነ የተጫዋች ቅጣት እንዲታገድለት አቤቱታውን ለኢ/እ/ፌ አሰምቷል።

ባሳለፍነው ሳምንት በተጠናቀቀው የ17ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች ድንጋይ ወደ ሜዳ ስለመወርወራቸው ሪፖርት ቀርቦ የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር ሃያ አምስት ሺህ እንዲከፍል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራር እና ስነስርዓት ኮሚቴ ማሳወቁ ይታወቃል።

ድሬዳዋ ከተማ በዚህ እና በሌሎች ጉዳዮች የተወሰነውን ውሳኔ መነሻ በማድረግ አቤቱታውን በዝርዝር አሰምቷል። ይህውም “በስታዲየሙ ተመልካቾች የውሃ መጠጫ ኮዳ ይዞ ወደ ሜዳ እንዳይገባ ተደርጎ ምንም አይነት ድንጋይ ወደ ሜዳው ሳይወረውር ጨዋታው በዲኤስ ቲቪ የቀጥታ ሽፋን የተተላለፈ በመሆኑ በግልፅ የሚታይ ሆኖ ሳለ በደፈናው ያለ ምንም ማስረጃ የውድድር ስነ ስርዓት ኮሚቴው ያስተላለፈብን የገንዘብ ቅጣት ተቀባይነት የለውም። በዚህም የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግልን እንዲሁም የክለባችን ተጫዋች አቤል አሰበ ያለ ምንም አይነት ጥፋት የተወሰነበት የአንድ ጨዋታ ቅጣት ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ቅጣቱ እንዲነሳልን እንጠይቃለን። ” በማለት ለፌዴረሽኑ የአቤቱታ የደብዳቤ ማቅረቡን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አሳውቋል።