የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ስብስቧን ይፋ አርጋለች


ያለፉትን ቀናት በርካታ ተጫዋቾን በመያዝ ከኢትዮጵያ ጋር ለሚደረጉት ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ስትዘጋጅ የነበረችው ሌሶቶ የመጨረሻ ተጫዋቾቿን ይፋ አርጋለች።

ቀጣዩ ሳምንት አህጉር አቀፍ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች የሚደረጉበት ወቅት እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በዚህ ወቅት ይፋዊ የነጥብ ጨዋታዎች የሚያደርግበት መርሐ-ግብር ባይኖረውም ራሱን ለመገምገም ከሌሶቶ አቻው ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።

በአሠልጣኝ ሌስሊ ኖትሲ የሚመሩት አዞዎቹ ከቀናት በፊት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በመጥራት ዝግጅት ጀምረው የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ ለሚደረጉት ሁለቱ ጨዋታዎች 23 ተጫዋቾችን ለይተዋል። በዚህም ሦስት የግብ ዘብ፣ ሰባት ተከላካዮች፣ አስር አማካዮች እንዲሁም ሦስት አጥቂዎች ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ይፋ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል እስካሁን የተጫዋቾች ምርጫም ሆነ ጨዋታው የት ስታዲየም እንደሚደረግ የወጣ መረጃ የለም። ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሰረት ግን ምናልባት ለውጦች ከሌሉ ሁለቱም ጨዋታዎች በመዲናችን አዲስ አበባ የሚከናወኑ ይሆናል።

የኢትዮጵያ እና ሌሶቶ ጨዋታዎች መጋቢት 12 እና መጋቢት 15 እንደሚከናወኑ ይጠበቃል።