ኡመድ ዑኩሪ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰበትን ዝውውር አገባዷል

በኦማን ሊግ ቆይታ ያደረገው ኡመድ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሰበትን ዝውውር ከደቂቃዎች በፊት ፈፅሟል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጫወት ከሀገራችን የስፖርት ቤተሰብ ጋር መተዋወቅ የቻለው ኡመድ ዑኩሪ 2006 ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ከፈፀመ በኋላ ወደ ግብፅ ሊግ በማምራት ለአሊተሀድ አሌክሳንድሪያ፣ ኤን ፒፒ፣ አል ኢታንግ አል አረቢ፣ ሶሞሀ እና አስዋን ለተባሉ ክለቦች ስድስት ዓመት ከግማሽ በማሳለፍ በ2013 አጋማሽ ወደ ሀገሩ በመመለስ በሀድያ ሆሳዕና መለያ ቆይታ አድርጎ ዓምና ወደ ኤሲያ በማምራት ለኦማኑ አል-ሱዋይክ ፊርማውን ማኖሩ አይዘነጋም።

በውዝግብ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ያገለለው አጥቂው አሁን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለሀዲያ ሆሳዕና የአንድ ዓመት ፊርማውን ማኖሩ ታውቋል። ተጫዋቹም በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ ፊርማውን ማኖሩ ታውቋል።