መረጃዎች | 72ኛ የጨዋታ ቀን

em>በ18ኛ ሳምንት ሶስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚደረጉ ሁለት መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ አቅርበናል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በደረጃ ሰንጠረዡ በተለያየ ፅንፍ የሚገኙትን ሁለት ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚው መርሃግብር ነበር።

ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድገው አብዛኛው ጊዜያቸው በወራጅ ቀጣናው ያሳለፉት ሻሸመኔ ከተማዎች ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ላይ ከሽንፈት ርቀው ውስን መሻሻል ቢያሳዩም በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ግን በፈለጉት የውጤታማነት ጉዞ ላይ አይገኙም።

ሆኖም ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማን ከገጠሙባቸው ጨዋታዎች የወሰዷቸው አራት ነጥቦች በ13ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው መድን ያላቸውን የነጥብ ልዩነት እንዲያጠቡ አስችሏቸዋል።

በነገው ጨዋታም ነጥብ ማግኘት ቢያንስ ለቀናት በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከውራጅ ቀጠናው የመውጣት ዕድል ስለሚያስገኝላቸው ጨዋታው ከፍ ባለ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ሆኖም ተጋጣሚያቸው በሂደት ወደ ጥሩ ብቃት የመጣውና ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደመሆኑ ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ህልማቸው ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ለውጥ የሚያስፈልገው ይመስላል።

ወደ ሊጉ መሪነት ዳግም ለመመለስ በጥረት ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ከአስራ አንድ ሳምንታት በኋላ ወደ መሪነት ይመለሳሉ።

ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች ውስጥ አስራ ሦስቱን በማሳካት በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ችለዋል። ይህንን ተከትሎም ደረጃቸውን ከማሻሻል ባለፈ መሪዎቹን እግር በእግር በመከተል ላይ ይገኛሉ።

ቡድኑ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ዓይነተኛ ተዋናይ የሆነው ንግድ ባንክን ጨምሮ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን ገጥሞ ያሳካቸው ድሎች ከሳምንታት በፊት ገጥሞት ከነበረው ውስን የወጥነት ችግር ወጥቶ መሻሻሎች እንዳሳየ አመላካች ናቸው።

ቡድኑ ተከታታይ ነጥብ በሰበሰበባቸው አምስት ሳምንታት አስር ግቦች አስቆጥረው በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ መረባቸውን ያስደፈሩት ፈረሰኞቹ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ቡድንን እየገነቡ ይገኛል። በተለይ በተለያዩ መንገዶች የሚያገኟቸው የግብ አማራጮች በተጋጣሚ በቀላሉ እንዳይገመቱ አድርጓቸዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጉዳት ላይ የሚገኘው ወጣቱ አጥቂ አሮን አንተር ከጉዳቱ ባለማገገሙ በነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ የጀመረው ተገኑ ተሾመ ምንም እንኳን ልምምድ ቢጀምርም በነገው ጨዋታ የመሳተፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። በአንፃሩ በሻሸመኔ ከተማ በኩል ወጋየሁ ቡርቃ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ታውቋል።

በሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው በሁሉም ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያሸንፍ 5 አስቆጥሮ ሻሸመኔ 2 አስቆጥሯል። ዘንድሮ ከሊጉ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ዋንጫ 2ኛ ዙር ተገናኝተው ፈረሰኞቹ 5-2 ማሸነፋቸው ይታወሳል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፉ የሚገኙትን ወልቂጤ ከተማዎችን በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ከፈፀሙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጋር ያገናኛል።

በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች አሁን ላይ በሊጉ በ11 ነጥቦች 15ኛ ላይ የሚገኙ ሲሆን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ የተጋሩ ሲሆን ይህም ውጤት ቡድኑ በውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ድላቸውን ካሳኩ 10 የጨዋታ ሳምንታትን የደፈኑበት ነበር።

ለወራት ለተጫዋቾች ካልተከፈለ ደሞዝ መነሻነት በብዙ ውጥረቶች ውስጥ የሚገኘው ቡድኑ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት የተቀዛቀዘ ጊዜን እያሳለፉ ሲገኝ አሁን ላይ የተጋረጠባቸውን ያለመውረድ ስጋት ለማስወገድ በቀጣይ ከፍተኛ የቤት ስራ ከፊታቸው እንደሚጠበቃቸው ይታመናል።

በአንፃሩ በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመሩት እና በሊጉ እስካሁን በ11 (64%) ጨዋታዎች የአቻ ውጤቶችን በማስመዝገብ በሊጉ በርካታ የአቻ ውጤቶችን በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አሁንም በወጥነት ጨዋታዎች ለማሸነፍ እየተቸገሩ እንደሆነ እያስተዋልን እንገኛለን።

አሁን ድረስ ከጥንቃቄ መር አጨዋወት በዘለለ በነፃነት ደጋግሞ ዕድሎችን በመፍጠር ሆነ ተጋጣሚን ጫና ውስጥ ከቶ በመጫወት ረገድ በብዙ መልኩ ውስንነቶች ያለባቸው ሀዲያ ሆሳዕና የማጥቃት ጨዋታቸው ላይ ተጨማሪ አቅምን ለመጨመር የቀድሞ ተጫዋቻቸው የሆነውን ዑመድ ዑኩሪን ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸው ለማጥቃታቸው የተለየ አድማስን እንደሚጨምር ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በሀዘን ምክንያት ቡድኑን ነገ በሜዳው ጠርዝ እንደማይመራ ሲረጋገጥ ተከላካዩ ወንድማገኝ ማዕረግ ደግሞ በጉዳት ምክንያት መሰለፉ አጠራጣሪ ነው በአንፃሩ በሀዲያ ሆሳዕና በኩል መለሰ ሚሻሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ስድስት ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲጠናቀቁ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ የተቀረችውን አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል። በጨዋታዎቹ ነብሮቹ ስድስት ሠራተኞቹ ደግሞ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 ውድድር አልተካተተም)