ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | በሦስት ጨዋታዎች 14 ግቦች ተመዝግበዋል

በምድብ “ለ” የሁለተኛው ዙር የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው አርባምንጭ ከተማ፣ ሸገር ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ ድል ቀንቷቸዋል ።

ረፋድ 3:00 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ወሎ ከተማን በሰፊ ግብ ድል አድርጓል።

አርባ ምንጭ ከተማ ፍፁም የበላይነት ባሳየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በአንፃሩ የወሎ ኮምቦልቻ በተደጋጋሚ የኳስ ቅብብል ሲበላሽ እና ሲቆራረጥ ተመልክተናል። በጨዋታው 4ኛ ደቂቃ ላይ የአርባምንጭ ከተማ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አህመድ ሁሴን ከእንዳልካቸው መስፍን የተላከለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላም አርባምንጭ ከተማ ይበልጥ ኳስን በመያዝ ጨዋታውን ሲቆጣጠሩ ተስተውሏል። ወሎ ኮምቦልቻ ግብ ከተቆጠረበትም በኋላም ምንም አይነት ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት አይታይባቸውም። አጋማሹም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በአርባምንጭ የበላይነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጭ ከተማ ከመጀመሪያው አጋማሽ ይበልጥ ጫና የፈጠረበት እና ተደጋጋሚ የግብ ዕድል የፈጠረበት አጋማሽ ነው። በ67ኛው ደቂቃ የአርባምንጭ ተጫዋች የሆነው ፍቃዱ መኮንን በጥሩ ቅብብል ወደ ወሎ ኮምቦልቻ የግብ ክልል በመግባት በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሯል። ከግቧ መቆጠር በኋላም አርባምንጭ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ባረጉት ጥረት በ75ኛው ደቂቃ ሳሙኤል አስፈሪ ከጥልቀት ኳስን ይዞ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመግባት ለአህመድ ሁሴን ያቀብላል ተብሎ ሲጠበቅ ራሱ ወደ ግብ በመግባት አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ማጠናከር ችሏል። ከሦስተኛው ግብ መቆጠር በኋላ ወሎ ከተማ እጅ በመስጠት ችለዋል። ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ በአርባ ምንጭ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ቡታቃ ሻመና ከመስመር የተሻገረውን ኳስ አስቆጥሮ ጨዋታው በአርባ ምንጭ ከተማ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 5:30 ላይ በተደረገው መርሀግብር ሸገር ከተማ ከፋ ቡና ላይ ግማሽ ደርዘን ግብ አስቆጥሮ አሸንፏል ።

የመጀመሪያው አጋማሽ እንደተጀመረ የሸገረ ከተማ ጫና ማሳደር ጀምሮ በ5ኛው ደቂቃ በተገኘው የማዕዘን ምት ተሻምቶ የከፋ ቡና የፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ በተደረገ ቅብብል ሲሳይ ጥበቡ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ሸገር ከተማ የተደናገጠውን የከፋ ቡናን የተከላካይ ክፍል በመረበሽ በ17ኛው ደቂቃ ፋሲል አስማማው ከአላዛር ሽመልስ የተቀበለውን ኳስ አስቆጠሮ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ሙሉ በሙሉ ጨዋታው በሸገር ከተማ የበላይነት የቀጠለው ጨዋታ በ31ኛው ደቂቃ የመሀል ሜዳ ተጫዋቹ ብሩክ ሰማ ግልፅ የግብ እድል ለተፈራ አንለይ በማመቻቸት ተፈራ አንለይ በጥሩ ሁኔታ አስቆጥሮ ከፋ ቡናን ተስፋ ማስቆረጥ ችሏል። አጋማሹም በዚው ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አጋማሽ የሸገር ከተማ የበላይነት እና የከፋ ቡና ፍፁም ደካማ አቋም አስመልክቶናል። በ57ኛው ደቂቃ የሸገር ከተማ ተጫዋች አላዛር ሽመልስ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ተከላካይ ቀንሶ በማስቆጠር የግብ መጠኑን ከፍ አድርጓል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሸገር ከተማ በርከት ያለ ተጫዋች ሲቀይር ተስተውሏል። ተቀይሮ የገባው መሐመድ ኑረዲን በ78ኛው ደቂቃ የተጋጣሚን ተከላካይ በመቀነስ አስቆጥሯል። በ87ኛው ደቂቃ መሐመድ ኑረዲን በራሱ ጥረት አስቆጥሮ ጨዋታው በሸገር ከተማ 6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቀን 7:30 ላይ የተደረገው ሦስተኛው ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ አዲስ ከተማ ክ/ከተማን አሸንፏል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሚባል አጨዋወትን ተመልክተናል። ጋሞ ጨንቻ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የአዲስ ከተማ ክ/ከተማን የግብ ክልል ሲፈትሹ ተስተውሏል። በ34ኛው ደቂቃ ጋሞ ጨንቻ ተጫዋች የሆነው ጌታሁን ገዛኸኝ በጥሩ ቅብብል ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። አጋማሹም በጋሞ ጨንቻ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጋሞ ጨንቻ ከመጀመሪያው አጋማሽ የበለጠ ተጠናክረው ገብተው ጫና ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ በኩል ኳስ ቶሎ ቶሎ ሲበላሽ እና ሲሳሳቱ ተስተውሏል። በ66ኛው ደቂቃ የጋሞ ጨንቻው ታደለ ቴንታ ተሻጋሪ ኳስን በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል። በ79ኛው ደቂቃ ያሬድ መኮንን በራሱ ጥረት አስቆጥሮ የግብ መጠኑን ከፍ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም በጋሞ ጨንቻ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።