ሪፖርት | ፈረሰኞቹ የሊጉን አናት ተቆናጠዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአማኑኤል ኤርቦ ሁለት ጎሎች ሻሸመኔ ከተማን 2ለ0 በመርታት የደረጃ ሰንጠረዡ መሪ ሆኗል።

ሻሸመኔ ከተማ በሀዋሳ ባለፈው ሳምንት ሽንፈት ካስተናገደው ቡድናቸው የአራት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ አቤል ማሞ ፣ ጌትነት ተስፋዬ ፣ ያሬድ ዳዊት እና አብዱልቃድር ናስርን በኬን ሰይዲ ፣ ወጋየሁ ቡርቃ ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና እዮብ ገብረማርያም ሲተኩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሀምበሪቾው ድል አንፃር ታምራት እያሱን በሞሰስ ኦዶ በብቸኝነት ያደረጉት ለውጣቸው ሆኗል።

ፈጠን ያለ እንቅስቃሴን በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ መመልከት ብንችልም በሂደቶች ውስጥ ግን በእጅጉ የተቀዛቀዘውን አጨዋወት ተመልክተናል። ሻሸመኔዎች በእዮብ ገብረማርያም ደካማ ሙከራን በማድረጉ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ፈረሰኞቹ መሐል ለመሐል በሚደረጉ ሰንጣቂ ኳሶች እና በሁለቱም ኮሪደሮች በኩል በሽግግሮች ሲጫወቱ ዝግ ያለውን ጨዋታ በተሻለ ነብስ ለመዝራት ሲጥሩ ተስተውሏል። 5ኛው ደቂቃ ናትናኤል በጥሩ ዕይታ የሰጠውን ዳዊት ተፈጥሯዊ ባልሆነ እግሩ መቶ ኳሷን ግብ ጠባቂው ኬኒ ይዞበታል። 9ኛው ደቂቃ ላይም በቀኝ የሜዳው ክፍል ሔኖክ አዱኛ ነፃ ቦታ ላይ ለተገኘው ሞሰስ ሰጥቶት አጥቂው ኳሷን በግቡ አናት ላይ ሰዷታል።

ተጋጣሚያቸው ለማጥቃት ወደፊት ተስቦ በሚሄድበት ወቅት የሚተወውን ቦታ ረጃጅም ኳሶችን ተደራሽ በማድረግ ሻሸመኔዎች ለማጥቃት ቢዳዱም በጨዋታው ላይ ጥራት ያለውን የግብ ዕድል ለመፍጠር ግን በእጅጉ ደካሞች ነበሩ። ወረድ ያለ የጨዋታ ፉክክርን እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ 39ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ የሚያስቆጭ አጋጣሚን ፈረሰኞቹ አምክነዋል። ናትናኤል ከፍ አድርጎ በሻሸመኔ ተከላካዮች መሐል ለመሐል የሰጠውን ኳስ ሞሰስ ኦዶ በደረቱ አብርዶ ግብ ጠባቂው ኬን ሰይዲን ጭምር አልፎ ከመረብ አገናኛት ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ውጪ ልኳታል። ከ40ኛው ደቂቃ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ አማኑኤል ተርፉ ከገዛኸኝ ደሳለኝ ጋር ተጋጭቶ ባስተናገደው ጉዳት በብረክ ታረቀኝ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ባሉት ቀሪ ደቂቃዎች ምንም የተለየ ነገርን ሳንመለከት አጋማሹ ያለ ጎል ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ የጨዋታውን ሀያ ያህል ደቂቃዎች በእንቅስቃሴ አንፃር የጎላ ብልጫን ያሳየ ቡድን ያልተመለከተን ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተከላካይ ጀርባ እና በተለይ ደግሞ በሁለቱ የሻሸመኔ የክንፍ ቦታዎች በሄኖክ እና ቢኒያም ጫናን ከ65 ደቂቃዎች በኋላ ማሳደር ከጀመሩ በኋላ እጅግ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ተመልክተናል። ረጃጅም ኳስን ለአጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ በማድረስ የግብ ምንጫቸውን ለማግኘት ጥረትን ያደርጉ የነበሩት ሻሸመኔዎች የፈረሰኞቹን የተከላካይ ክፍል አልፈው ከመረብ ጋር መገናኘት ግን አልቻሉም።

ዳግማዊ እና ሞሰስን ፣ በአማኑኤል እና ታምራት በመተካት የአጥቂ ክፍላቸው ያደሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የቢኒያም እና ሔኖክ አዱኛን ሰርቪስ አልፎ አልፎ ደግሞ ረመዳንን በመጠቀም በርካታ የግብ ዕድሎች ቢያገኙም ከሚታይባቸው የስልነት ችግሮች አኳያ የተገኙ መልካም አጋጣሚዎችን በቀላሉ ሲያመክኑ ቆይተው ጫናዎቻቸውን ከፍ እያደረጉ ቀጥለው 70ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግን ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። ረመዳን ከግራ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ታምራት በግንባር ጨርፎ ከጀርባው የነበረው አማኑኤል ተርፉ አግኝቷት ኬኒ ሰይዲ መረብ ላይ አስቀምጧት ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ጎልን ካስቆጠሩ በኋላ በዳዊት ፣ ታምራት እና አማኑኤል አማካኝነት ዕድሎችን በተጨማሪነት ለመፍጠር አጠናክረው ቀጥለው 86ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ጎል አስቆጥረዋል። ቢኒያም በላይ ከግራ በጥሩ የእግር ስራ ሳጥን ውስጥ ይዞ የገባውን ኳስ ነፃ ሆኖ ለተገኘው አማኑኤል አቀብሎት አጥቂው ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎልን በማድረግ ጨዋታው በመጨረሻም በ2ለ0 የፈረሰኞቹ አሸናፊነት ተቋጭቷል። ውጤቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹ ሊጉን በ37 ነጥቦች መምራት ጀምረዋል።

ከጨዋታው መቋጫ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔ ከተማው ረዳት አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ ተመጣጣኝ እና ጥሩ ጨዋታ እንደነበር ጠቅሰው ዕድል ከቡድናቸው ጋር አለመኖሩንም የ57 ደቂቃ የሳትናት ኳስ ዋጋ አስከፍሎናል በጨዋታው ተጫዋቾቼን አልወቅስም ሲሉም ተደምጠዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ከባድ እና ጠንካራ ጨዋታ እንደነበር ተናግረው በመጀመሪያው አጋማሽ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል መድረስ ችለው ነገር ግን ባለ መረጋጋት መባከን መቻላቸውንም ከዕረፍት መልስ ግን በተደረጉ ቅያሪዎች ጎል በማስቆጠር አሸንፈው መውጣት መቻላቸውን በንግግራቸው ተናግረዋል።