ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ ያለመሸናነፍ ተገባዷል

የኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች አንድ አንድ ጎል እና አንድ አንድ ነጥብ በማስገኘት ተደምድሟል።

የምሽቱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከፋሲል ከነማ አገናኝቶ ቡናማዎቹ በ18ኛው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ 3ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ወንድሜነህ ደረጄ ፣ አሥራት ቱንጆ እና ብሩክ በየነን አስወጥተው ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ ኪያር መሐመድ እና አማኑኤል አድማሱን አስገብተዋል። ዐፄዎቹ በበኩላቸው በተመሳሳይ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር 2ለ2 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት ተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ ፣ መናፍ ዐዎል እና ፍቃዱ ዓለሙ በይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ ኤልያስ ማሞ እና ጌታነህ ከበደ ተተክተው ገብተዋል።

በጎል ሙከራዎች ረገድ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ስል ባይሆንም የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያስተናገደው በ15ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህ ደቂቃ መስፍን ታፈሰ ለቡናማዎቹ ሙከራ ከማድረጉ በፊት ደግሞ ዐፄዎቹ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው አማኑኤል ገብረሚካኤል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አማኑኤል በ20ኛው ደቂቃም ከግብ ዘቡ በረከት አማረ ጋር ተጋጭቶ ሁለቱም ለጉዳት በተዳረጉበት ሌላ አጋጣሚ ፋሲል ለግብ ቀርቦ ነበር።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ማስመልከት የያዘው ተጠባቂው ፍልሚያ በአማኑኤል እና በረከት ግጭት ለ8 ደቂቃዎች ተቋርጦ ሲቀጥል ሁለቱም የተጫዋች ለውጥ አድርገው ነበር። በተጫዋቾቹ ጉዳት የትኛው ቡድን ይጎዳል የሚለውን ሀሳብ ገና ሳይታለም በ31ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡና በለወጠው የግብ ዘብ ዋጋ ከፍሏል። በተጠቀሰው ደቂቃም አቤል እንዳለ ከወደ ቀኝ ከሚገኝ የሳጥኑ ክፍል መግቢያ ላይ ወደ ጎል የላከውን ቀለል ያለ ኳስ በረከትን ቀይሮ የገባው እስራኤል መስፍን መቆጣጠር ተስኖት ግብ ተቆጥሯል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት የያዙት ቡናማዎቹ በፍቃዱ ከግቡ በፊት እና በኋላ ከሰነዘራቸው ጥሩ ጥሩ ጥቃቶች በተጨማሪ በአጋማሹ መገባደጃ ላይ አቻ ለመሆን የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። ይህ ውጥናቸው ሰምሮም የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው 9ኛ ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ባስቆጠረው ኳስ ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በይሁን እንደሻው አማካኝነት ሙከራ ሰንዝረው ቀዳሚውን ጥቃት ያስመዘገቡት ፋሲሎች በአንፃራዊነት ከቡና በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ይዘዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በተቃራኒ በሁለተኛው አጋማሽ የተወሰደባቸውን መጠነኛ ብልጫ እየተቋቋሙ እድገት ለማሳየት ጥረው በ58ኛው እና 59ኛው ደቂቃ ተከታታይ የሰሉ ሙከራዎች አድርገዋል። በመጀመሪያው አጋጣሚ አብዱልከሪን የቡድኑን ሙከራ ሲያደርግ ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ የግቡ ባለቤት መስፍን ከአብዱልከሪም የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ልኮ ነበር።

የቡናማዎቹ የፊት አውራ መስፍን ለፋሲሎች ስጋት በመሆን ተከታታይ ሙከራዎችን ሲሰነዝር ነበር። ጨዋታው 77ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ደግሞ የበረከትን አምበልነት የተረከበው ዋሳዋ ጂኦፍሪ ጥብቅ ምት ወደ ግብ በመላክ ቡድኑን ወደ መሪነት ለማሸጋገር ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኪ በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። ከደቂቃ በኋላም የግራ መስመር ተከላካዩ በፍቃዱ ሌላ ጥራት ያለው ሙከራ አድርጎ ሳማኪ በጥሩ ብቃት ቡድኑን በጨዋታው እንዲቆይ አድርጓል። እንደ አጀማመራቸው ያልዘለቁት ፋሲሎች በ83ኛው ደቂቃ እጅግ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ በሽመክት ጉግሳ አማካኝነት ፈጥረው የግቡ ቋሚ ግብ እንዳያገኙ ከልክሏቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት አንድ አቻ ተፈፅሟል።

ከጨዋታው በኋላ የኢትዮጵያ ቡናው ምክትል አሠልጣኝ ታፈሰ ተስፋዬ ሁለት ጨዋታ ተሸንፈው እንደመምጣታቸው ተጫዋቾቹ ላይ ውጥረት እንደነበር በማንሳት ያገኙት አንድ ነጥብ እንደማያስከፋ አመላክተዋል። የፋሲል ከነማው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ጨዋታው ጠንካራ እንደነበር በማመላከት መሪ ከሆኑ በኋላ የተጫወቱት አጨዋወት ጥሩ እንዳልነበር እንዲሁም ያገኟቸውን የግብ እድሎች መጠቀም ላይ አሁንም ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።