ከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነቱን አጠናክሯል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ”ሀ” 18ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዲስ አበባ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።


ረፋድ ሦስት ሰዓት ላይ በተደረገው መርሐግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኮልፌ ቄራኒዮን ገጥሞ ከፍፁም የጨዋታ የበላይነት ጋር በሰፊ ግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል። ገና ጨዋታው ከመጀመሩ ግቦችን ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ግብ ክልል ሲገቡ የቆዩት ኤሌክትሪኳች የመጀመሪያ ግብ ለማስቆጠር 8 ደቂቃ ነበር የጠበቁት። በ8ኛው ደቂቃ አቤል ሀብታሙ በመስመር በኩል ሆኖ  ያሻገረለትን ኳስ መሳይ ሰለሞን በ8ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር መሪ አድርጓቸዋል። በዚህ ብቻ ያላበቁት ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ኮልፌዎች በአንፃሩ ደካማ የኳስ ቁጥጥር ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። በተደጋጋሚ የኮልፌን ግብ ለመድፈር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ግብ በ38ኛው ደቂቃ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው በአቤል ሀብታሙ አማካኝነት አግኝተዋል። በ38ኛው ደቂቃ ናትናኤል ሰለሞን ከመሃል ሜዳ የሰነጠቀለትን ኳስ አቤል ሀብታሙ  በግሩም አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ኮልፌዎች በመነቃቃት የተጫወቱ ሲሆን ግቦችን ለማስቆጠርም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ጫና አሳድረዋል። ሆኖም ግን ነጥቡን ለማስጠበቅ እና መሪነቱን ለማስቀጠል ምንም እንኳን ደካማ የኳስ ቁጥጥር ቢያደርግም በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ሆኖ የሰነበተውን ኤሌክትሪክ ተከላካይ መስመር ደፍሮ ግብ ለማስቆጠር ቸግሯቸዋል። ኮልፌዎች መድረሻቸውን የፊት መሰመር አጥቂው ኤልያስ ላይ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል ግብ ለማስቆጠር የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ አድርገዋል። ኤሌክትሪክም በመልሶ ማጥቃት የግብ ሙከራ አድርጓል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተቀይሮ የገባው ልዑልሰገድ አስፋው በአንድ ለአንድ ቅብብል በመግባት ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ሶስተኛ ግብ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጨዋታው 3ለ0 እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

ሁለኛው የዕለቱ ጨዋታ 10:00 ላይ በአዲስአበባ ከተማ እና ሞጆ ከተማ መካከል ተደርጎ አዲስ አበባ ከተማ በሁለተኛው አጋማስ በተቆጠረ ብቸኛ ግብ ድል አድርጓል።


እምብዛም የግብ ሙከራ ባላስመለከተው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ግብ እንዳይቆጠርባቸው በጥንቃቄ ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ጨዋታው ከመጀመሩ በ13ኛው ደቂቃ የሞጆ ከተማው ኢዮብ አለሙ በአዲስ አበባው ቢኒያም ፀጋዬ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ጨዋታው አንድ ጎን እንዲይዝ ቢያደርግም ሞጆ ከተማዎች ምንም እንኳን በጎዶሎ ለመጫወት ቢገደዱም በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የሆኑበትን አርባ አምስት አሳልፈዋል። አዲስ አበባ ከተማም በአንፃሩ ክፍተቱን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ ለመመለከት ተችሏል። ሆኖም ግን አስቆጪ የሚባሉ ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች አግኝተው በደካማ አጨራረስ ሲያመክኑ ተስተውለዋል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ሊጠናቀቅ ግድ ሆኗል።

ከዕረፍት መልስ አዲስ አበባ አንዳንድ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብሎ ሲገባ ሞጆ ከተማ 10 ተጫዋች በመሆናቸው እና የተጫዋች ብልጫ ስለተወሰደባቸው ወደ ኋላ በመመለስ ሲከላከሉ ለማየት ተችሏል። ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በ47ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ኤርሚያስ ኃይሉ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ አዲስ አበባ ከተማን መሪ አድርጓል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ወደ ጨዋታው የተመለሱት አዲስ አበባዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል። ሞጆ ከተማም በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ደካማ የኳስ ቁጥጥር አደርጓል። ሆኖም ግን ተጨማሪ ግብ እንዳይቆጠርበት በመካለከል አልፎ አልፎም በመልሶ ማጥቃት የግብ ማግባት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ቢሆንም ጨዋታው በኤርሚያሰ ኃይሉ ብቸኛ ግብ አዲስ አበባ ከተማን አሸናፊ አድርጎ ተገባዷል።