ሪፖርት | አለልኝ አዘነን ባወሱበት ጨዋታቸው የጣና ሞገዶቹ ዘጠነኛ የሊግ ድላቸውን አሳክተዋል

ባህር ዳር ከተማዎች በቸርነት ጉግሳ ብቸኛ ጎል ሻሸመኔ ከተማን 1ለ0 በመርታት ተከታታይ ሦስተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

የጣና ሞገዶቹ በ18ኛው ሳምንት የሊጉ መርሐግብራቸው ኢትዮጵያ ቡናን 3ለ1 በረቱበት ወቅት ከተጠቀሙት ቋሚ 11 መካከል ሙጂብ ቃሲምን በፍፁም ጥላሁን በብቸኝነት ያደረጉት ለውጥ ሲሆን በሲዳማ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት 1ለ0 ሽንፈት አስተናግደው በነበሩት ሻሸመኔ ከተማዎች በኩል በተደረጉ ሁለት ቅያሪዎች ምንተስኖት ከበደን በአሸብር ውሮ ፣ አሸናፊ ጥሩነህን በኢዮብ ገብረማርያም ተክተዋቸል።

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቻቸው የነበረውን አለልኝ አዘነን ከቀናቶች በፊት በድንገተኛ ህልፈት ያጡት ባህር ዳር ከተማዎች ተጫዋቹን የሚዘክሩ ስነ ስርዓቶችን ካከናወኑ በኋላ በሕሊና ጸሎት ጨዋታው በሚካኤል ጣዕመ መሪነት ተጀምሯል። ፈጠን ያሉ ቅብብሎች በታዩበት የምሽቱ ጨዋታ ባህር ዳሮች የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን በመያዝ ወደ ግራ በይበልጥ ባመዘነ እንቅስቃሴ ለመጫወት በሞከሩበት ወቅት 8ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ቸርነት በቀጥታ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ ብረት በኩል  ታካ ወጥታለች።

ከራስ ሜዳ በረጅሙ አጥቂዎቻቸውን የሚፈልጉ ኳሶችን በመጣል እና ከግራ ኢዮብ ወደ ውስጥ በሚጥላቸው ተሻጋሪ የግንባር ኳሶች ጎልን ለማስቆጠር የጨዋታ መንገዳቸውን ያደረጉት ሻሸመኔዎች 10ኛው ደቂቃ በረጅሙ ወደ ተከላካይ ስፍራ የተላከን ተንጠልጣይ ኳስ አብዱልቃድር በግንባር ገጭቶ ያመቻቸለትን አብዱልከሪም በጥሩ የዓየር ላይ ኳስ ሲመታት ፔፕ ሰይዶ ተቆጣጥሮበታል።

በተሻለ ተነሳሽነት መሐል ሜዳ ላይ ከሚደረጉ ንክኪዎች በኋላ የቀኝ የሻሸመኔን የግብ ክፍል በመጠቀም የበላይነትን ወስደው መጫወታቸውን የቀጠሉት የጣና ሞገደኞቹ ፍራኦል ከማዕዘን አሻምቶ ቸርነት በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት እና ቸርነት ከርቀት አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ከተባለበት በኋላ ጨዋታው 23ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ አለልኝ የሚለብሰውን መለያ በማስታወስ ጭብጨባዎች በስታዲየሙ ከተደረጉ በኋላ 39ኛው ደቂቃ ላይ ባህር ዳሮች ጎል አስቆጥረዋል። ከሻሸመኔ ተጫዋቾች የተቋረጠን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ አግኝቶት በመጨረሻም ጥሩ አድርጎ ያመቻቸለትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ከሳጥን ውጪ ግሩም ጎልን ኬን ሳይዲ መረብ ላይ አሳርፎ ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 1ለ0 መሪነት ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከመልበሻ ቤት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ቸርነት በጥልቀት ለማጥቃት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የመሳይ አገኘሁን የቀኝ መስመር በመጠቀም ተጨማሪ ዕድሎችን ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ ሲሆን ከቅጣት ምት ፍራኦል ካደረጋት ሙከራ እና ኬን ሳይዲ ከተቆጣጠረበት አጋጣሚ መልስ ሻሸመኔ ከተማዎች 59ኛው ደቂቃ አብዱልቃድር ናስር እና ሔኖክ ድልቢን በስንታየሁ መንግሥቱ እና ጌትነት ተስፋዬ በመተካት በቅያሪዎቻቸው ዕገዛ በሽግግር ወደ ጨዋታ ለመመለስ በነበራቸው የተወሰነ መነቃቃት አከታትለው አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል።

67ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ አንድ ሁለት አብዱልከሪም ከጌትነት ጋር ተጫውቶ ከግራ ጌትነት ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት የሰጠውን ኳስ ስንታየው ከግቡ ትይዩ ሆኖ ሲመታው ፔፕ ሰይዶ ሲያድንበት በድጋሚ ቁመታሙ አጥቂ ኳሷን ተቆጣጥሮ ፍራኦል እና ያሬድን አልፎ ወደ ጎል  ቢሞክርም ንቁ በነበረው የግብ ዘብ ፔፕ ሰይዶ መክኖበታል። ጥሩ ፉክክርን እያየንበት ጨዋታው ቢቀጥልም የጠሩ ዕድሎችን ለማየት በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ያልታደልንበት ሲሆን ሻሸመኔዎች አቻ ሆኖ ጨዋታው ለመጨረሽ ቶሎ ቶሎ መዳረሻቸውን ወደ ሳጥን ባደረጉ የዓየር ላይ ኳሶች ባህር ዳር ከተማዎች መሐል ሜዳውን ከመስመር ተጫዋቾች ጋር በማቀራረብ ሲጫወቱ ከመታዘብ ውጪ አጋጣሚዎች እምብዛም ሳይፈጠሩበት በባህር ዳር ከተማ 1ለ0 ድል አድራጊነት ጨዋታው ተደምድሟል። ድሉን ተከትሎ የጣና ሞገዶቹ ደረጃቸውን ወደ 5ኛ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀራቸው ከፍ አድርገዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሻሸመኔ ከተማው ረዳት አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ ስንከላከል ጥሩ ነበርን ካሉ በኋላ ለማጥቃት ጥረት በሚደረግበት ወቅት  ጎል እንዳስተናገዱ እና ጨዋታውም ጥሩ እንደነበር ጠቁመው ተጫዋቾቻቸውን በማመስገን ያቀዱት ዕቅድም መሳካቱን በንግግራቸው አውስተዋል። የባህርዳር ከተማ አቻቸው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቡድኑ ከነበረበት ለመውጣት እና ካሳለፉት የሀዘን ድባብ ለመውጣት ሜዳ ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ መቻሉን ከገለፁ በኋላ ሦስት ነጥብ ለማሳካት እና አለልኝን ለመዘከር ተጫዋቾቻቸው  አሸንፈው ለመውጣት ያደረጉትን ጥረት አድንቀው አመስግነዋል።