ሪፖርት | የተጠበቀውን ያህል ፉክክር ያልታየበት ጨዋታ ያለ ጎል ተቋጭቷል

መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ጥራት ያላቸው ሙከራዎች ተበራክተው ሳናስተውል 0ለ0 ተጠናቋል።

መቻሎች ወላይታ ድቻን ባለፈው የጨዋታ ሳምንታቸው ሲረቱ የተጠቀሙትን የመጀመርያ 11 ሳይቀይሩ ወደ ሜዳ ሲገቡ በአዳማ ከተማ ሽንፈት በገጥሟቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በተደረገ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አማኑኤል አረቦን ከጉዳት በተመለሰው ተገኑ ተሾመ በብቸኝነት ያደረጉት ለውጥ ሆኗል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሠ መሪነት በጀመረው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ከሙከራዎች ይልቅ የእንቅስቃሴ መበራከቶች የበዙበት ነበር። በተሻለ አቀራረብ መሐል ሜዳው ላይ አመዝነው  ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት መቻሎች ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ከመሐል መነሻቸው ካደረጉ አልያም ከመስመሮች በኩል ሰብሮ ለመግባት በሚደረጉ ቅብብሎች ሙከራዎችን ለማድረግ በተወሰነ መልኩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ማየት ብንችልም እንደነበራቸው ብልጫ ብዙም ዕድሎች ፈጥረው አልተመለከትንም። 19ኛው ደቂቃ ላይ ከመሐል ክፍሉ ዮሐንስ መንግስቱ ተከላካዮች መሐል ላይ የጣለለትን ኳስ ሽመልስ በቀለ ከተቆጣጠራት በኋላ ወደ ጎል መቶ የግብ ዘቡ ባህሉ ነጋሽ ሲተፋው አቤል ነጋሽ እግሩ ስር ኳሷ ደርሳው ቢመታምም በግቡ ቋሚ ብረት ታካ ልትወጣ ችላለች።

ጨዋታውን ዝግ ባለ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሆን በሽግግር ወደ መስመር በማድላት ሲጫወቱ የተመለከትናቸው ፈረሰኞቹ በዚሁ የአጨዋወት መንገድ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ደርሰው ልዩነት ለመፍጠር ተቸግረው ከቆዩ በኋላ 21ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መነሻውን አድርጎ ኳስን ሁለት ጊዜ ገፋ በማድረግ አጥቂው ሞሰስ ኦዶ ከሳጥኑ ጠርዝ ወደ ግብ የመታው ኳስ አሊዮንዚ ናፊያን በቀላሉ ተቆጣጥሮበታል። 33ኛው ደቂቃም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሳጥን ውስጥ ዳዊት ተፈራ የያዛትን ኳስ በጥሩ ዕይታ ወደ ቀኝ ያቀበለውን ሔኖክ አዱኛ ሞክሮት የግቡን የላይኛው አግዳሚን ኳሷ ለትማ ወደ ውጪ ወጥታለች። ከተጠባቂነቱ አንፃር ጥራት ያላቸው ሙከራዎች በዝተው ያልተመለከትንበት የቡድኖች ቀዝቀዝ ያለ መልክ የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል ጨዋታው አምርቷል።

ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው ሲቀጥል ወረድ ያሉ ፉክክሮችን እያስመለከተን ቀጥሎ ሜዳ ላይ ልዩነት ለመፍጠር ከሚደረጉ ትጋቶች ይልቅ የተዳከመውን ሁለተኛ አጋማሽ መመልከት ችለናል። የኋሊዮሽ ቅብብሎች የበዙበት ከመሆኑ አኳያ ወደ ግብ ደርሶ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን  ለማየት በናፈቀን ቀጣዮቹ የቡድኖች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ከተደረጉ የተጫዋች ቅያሬዎች ውጪ ትኩረትን የሚስቡ የጨዋታ ብልጫ እና የግብ ዕድሎች ተፈጥረው አላስተዋልንም። 68ኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ ዳዊት ተፈራን በዳግማዊ አርዓያ በጦሩ በኩል ደግሞ 73ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ እና ከነዓን ማርክነህን ወጥተው በበረከት ደስታ እና በአብዱ ሞቶሎባን መተካት የቻሉበት ሂደት ይጠቀሳል።

በአጋማሹ ናትናኤል ዘለቀ 75ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ደካማ ሙከራን አድርጎ አሊዮንዚ በቀላሉ ከያዘበት ሙከራ ውጪ የተዳከሙ  አቀራረቦችን እያስተዋልን ተጉዘን የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች በፊት መስመራቸው ላይ ዕድሳት ያደረጉት መቻሎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት እና መሐል ለመሐል በሚሾልኩ ኳሶች ብልጫውን መያዝ ቢችሉም የቅዱስ ጊዮርጊስን አጥር አልፈው ግብ በማግኘቱ ረገድ ያልተሳካላቸው ሲሆን ፈረሰኞቹም በመልሶ ማጥቃት በተሻጋሪ ኳሶች በጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥ ያደረጓቸው ደካማ  ጥረቶች ፍሬ አፍርተው ሳንመለከት በጥቅሉ ደብዛዛ እንቅስቃሴዎችን ያየንበት ጨዋታ ያለ ጎል መጠናቀቅ ችሏል።

ከጨዋታው መቋጫ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታው መጥፎ እንዳልሆነ ጠቁመው ጥንቃቄ እና ታክቲክ የታየበት እንደሆነ ጠንካራ ፉክክርም እንደተደረገበት ውጤቱም በአጠቃላይ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የመቻሉ ረዳት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ በበኩላቸው ጉጉቶች እንደነበሩ የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ጎልነት ለመለወጥም ችኮላዎች እንደታዩ እና ለማሸነፍ ከነበራቸው ግምት አኳያም በሚፈለገው ደረጃ እንዲጫወቱ እንዳላደረጋቸው እና ውጤቱም የሚያስከፋ እንዳልሆነም በንግግራቸው ጠቁመዋል።