መረጃዎች| 80ኛ የጨዋታ ቀን

በ20ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን የሚደረጉ ተጠባቂ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

መቻል ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በላይኛው የደረጃ ሰንጠረዡ ክፍል የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ጦሩን ከፈረሰኞቹ ያገናኛል።

ከሁለት ሽንፈቶች አገግመው በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በማስመዝገብ በ2ኛ ደረጃነት የተቀመጡት መቻሎች የነገውን ጨዋታ አሸንፈው መሪነታቸውን ለማስመለስ ከባድ ፈተና ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።

ከአንድ የጨዋታ ሳምንት በፊት የቅርብ ተፎካካሪያቸው ንግድ ባንክን መርታት የቻለው ጦሩ በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ እርምጃ ለመራመድ እንደሚያቅድ እሙን ነው። ሆኖም ከተጋጣሚያቸው ቀላል ፈተና እንደማይገጥማቸው የታወቀ ነው። መቻሎች ድል ባደረጉባቸው ሁለት ጨዋታዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣት ችለዋል። ቡድኑ በሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ካስተናገደ በኋላ በብዙ ረገድ ተሻሽሎ ለወሳኙ ጨዋታ መድረሱም እንደ ትልቅ ለውጥ የሚታይ ነው። በነገው ጨዋታም ግብ ከማስቆጠር ከማይቦዝነው የፈረሰኞቹ የፊት መስመር ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ቢታመንም የኋላ መስመሩ የሚያደርገው አፀፋሚ ምላሽም ቀላል እንደማይሆን የባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴው ምስክር ነው።

መቻሎች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ጥሩ የሚባል የፊት መስመር ጥምረት ገንብተው በጨዋታዎቹ ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ሆኖም እንደሚፈጥሯቸው ዕድሎች በርካታ ግቦች ማስቆጠር አልቻሉም። በነገው ጨዋታም ተጋጣሚያቸው የመከላከል ጥንካሬ ያለውና እንደቡድን ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ውስጥ በቶሎ ቅርፁን በሚያግኝ ቡድን እንደመሆኑ ከላይ የተነሳው እና ድል ባደረጉባቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ የተስተዋለው የማጥቃት ዑደት በጥሩ አፈፃፀም ላይ መገኘት የግድ ይለዋል።

በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ሽንፈት አስተናግደው መሪነቱን የመረከብ ዕድላቸው ያባከኑት ፈረሰኞቹ ድል አድርገው በፉክክሩ ለመቆየት ወደ ሜዳ ይገባሉ። ፈረሰኞቹ ምንም እንኳ ከሳምንታት በኋላ ሽንፈት ቢያስተናግዱም በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ነበራቸው፤ ሆኖም በተጋጣሚ የሜዳ ክልል የነበራቸው የውጤታማነት ደረጃ ንፁህ የግብ ዕድሎች እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል። በጨዋታው ላይ የተጋጣሚን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ንፁህ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገረው ቡድኑ በነገው ዕለት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ጥንካሬ የተላበሰውና በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው መቻል ስለሚገጥም የባለፈው ጨዋታ ክፍተቱን አርሞ መቅረብ ግድ ይለዋል። የነገው ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የውድድር ዓመቱ ወሳኝ ጨዋታ ከመሆኑ አንፃር ከባለፉት ጨዋታዎች ለየት ያለ የፉክክር ደረጃ ያስመለክተናል ተብሎ ይገመታል።

የቡድን ዜናን ስንመለከት በመቻል በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ሲታወቅ ቶጎዋዊው አዲስ ፈራሚ አብዱ ሙታላቡ ኡታራንም ለነገው ጨዋታ እንደሚደርስ ተረጋግጧል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አምስት ቢጫዎች የተመለከተው አማኑኤል ኤርቦ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም።

መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ 33 ጊዜ ሲገናኙ 36 ግቦችን ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ 12 ጊዜ ድል ሲያደርግ 18 ግቦች ያሉት መቻል ደግሞ 3 ጊዜ አሸንፏል። ቡድኖቹ 18 ጊዜ ነጥብ የመጋራት ታሪክም አላቸው።

ባህር ዳር ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ምሽት ላይ ባህር ዳር እና ሻሸመኔን ያገናኛል።

ከአስከፊው አራት ተከታታይ ሽንፈት ወጥተው ድሎች ማጣጣም የቻሉት የጣና ሞገዶቹ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በትልቅ ደረጃ የሚጠቀስ መሻሻል አሳይተዋል። ቡድኑ በተጠቀሱት ሳምንታት ሦስት ድልና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ደረጃውን ከማሻሻል ባለፈ በእንቅስቃሴ ረገድም በጎ ለውጦች አሳይቷል። ከዚህ ባለፈ በዋንጫ ፉክክሩ ያሉትን ኢትዮጵያ ቡናና መቻልን ማሸነፉ ለመሻሻሉ ማሳያ ነው። በተለይም ጠንካራ የፊት መስመር ያላቸውን ቡድኖች ገጥሞ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በጉልህ የሚታይ በጎ ለውጥ አምጥቷል፤ አድናቆትም ይገባዋል። ሆኖም ቀላል የማይባል የተጫዋቾች ክምችት ያለው የፊት መስመር ከዚህ የበለጠ ስል መሆን ይኖርባታል። የፊት ጥምረቱ በመጨረሻው ጨዋታ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ከዛ በፊት በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን ግን ሁለት ብቻ ነበር። በነገው ጨዋታም ስልነቱ ማስቀጠል ይኖርበታል።

በአስራ ሁለት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሻሸመኔ ከተማዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ባህርዳር ከተማን ይገጥማሉ። ሻሸመኔ ከተማዎች ወላይታ ድቻን ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል። ቡድኑ ከሽንፈቱም በዘለለ በብዙ ረገድ ተቀዛቅዟል፤ በተለይም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት የባለፉት ሳምንታት ጥንካሬውን አጥቷል። በነገው ጨዋታም በሂደት ወደ ጥሩ የግብ ማስቆጠር ብቃት የመጣውን ባህር ዳር ከተማን እንደመግጠማቸው በሁሉም ረገድ ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

በባህር ዳር ከተማ በኩል ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። በሻሸመኔ በኩል ግን የአራት ጨዋታዎች ቅጣት የተላለፈበት ማይክል ኔልሰን በዚህ ጨዋታ አይሰለፍም።

ባህር ዳር እና ሻሸመኔ በሊጉ ባደረጉት የመጀመሪያ የእርስ በእርስ ጨዋታቸው ያለግብ ተለያይተው ነበር።