መረጃዎች | 87ኛ የጨዋታ ቀን

የ22ኛ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ ቀን መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ ተሰናድተዋል።

ሀምበሪቾ ከ ሀዋሳ ከተማ

የዕለቱ ቀዳሚው መርሃግብር በ22 ነጥቦች ልዩነት በ4 ደረጃዎች ተራርቀው የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች ያገናኛል።

በሊጉ ከ21 ሳምንታት በኃላ ስምንት ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሀምበሪቾዎች ይህም በሊጉ በብቸኝነት ባለ አንድ አሀዝ ነጥብ የሚገኙ ያደርጋቸዋል ፤ ይህም አሁን ላይ ቡድኑ በሊጉ ለመቆየት የሊግ ቆይታውን ከሚያረጋግጥለት የመጨረሻው ስፍራ እንኳን የአስራ አንድ ነጥብ ልዩነት የመኖር ጉዳይ የቤት ስራቸውን ከባድ ያደርግባቸዋል።

በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ጠንካራውን ፋሲል ከነማ ሳይጠበቅ ለመርታት ተቃርቦ የነበረው ቡድኑ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት የተገደዱ ሲሆን በጨዋታው ላይ ቡድኑ ያሳየው እንቅስቃሴ ከውጤቱ ባለፈ ተስፋ የሚሰጥ ነበር።

በመሆኑም በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ከጠንካራው ፋሲል ከነማ ያሳካት አንድ ነጥብን እንደመነሳሻ በመቆጠር በነገው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ከተከታታይ ሽንፈቶች መልስ የነገውን ጨዋታ የሚያደርጉት ሀዋሳ ከተማዎች በሰንጠረዡ በ26 ነጥቦች በሰንጠረዡ በ11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በመከላከሉ ረገድ በብዙ መልኩ ጥያቄዎች የሚነሳባቸው ሀዋሳ ከተማዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣት እንደ ሰማይ የራቃቸው ይመስላል ፤ በሊጉም ለመጨረሻ ጊዜ ይህን ማድረግ የቻሉት በመጀመሪያው ዙር የነገው ተጋጣሚያቸውን ሀምበሪቾን 2-0 በረቱበት ከሰባት የጨዋታ ሳምንታት በፊት በተደረገው መርሃግብር ነበር።

በማጥቃቱም ቢሆን አሁንም ቡድኑ ከዓሊ ሱሌይማን የግል ምትሃት ውጭ እንደ ቡድን እድሎችን በበብዛት እና ጥራት ከመፍጠር እንዲሁም ከማስቆጠር አንፃር ውስንነቶች ያሉበት ሲሆን ቡድኑ ለመጫወት የሚፈልገውን ምልልሶች የበዙበትን የጨዋታ ሂደት ተጋጣሚ የማይፈቅድ ከሆነ እንደ ቡድኑ ደካማ ቀንን ለማሳለፍ ሲገደዱ እያስተዋልን እንገኛለን።

ሀምበሪቾዎች በጉዳት ምክንያት የዳግም በቀለ እና ምናሴ ቢራቱን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች በኩል አብዱልበሲጥ ከማል ከቅጣት የሚመለስ ሲሆን የተቀሩት ተጫዋቾች ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ

የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ መምህሩን ከተማሪው የሚያገናኘው ጨዋታ ነው።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ፋሲል ከነማዎች በወጣ ገባዎች በተሞላው የውድድር ዘመናቸው አሁን ላይ በ32 ነጥቦች በሰንጠረዡ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ፤ ምንም እንኳን በሰንጠረዡ 4ኛ ደረጃ ከሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና እንኳን ያላቸው የነጥብ ልዩነት አንድ ቢሆንም እንኳን ቡድኑ ከሚጠበቅበት አንፃር እያሳየ ያለው አፈፃፀም በቂ ስላለመሆኑ መናገር ይቻላል።

በፋሲል በኩል በቅርብ ጨዋታዎች እየተመለከትን የምንገኘው አውንታዊ ጉዳይ ከቡድኑ የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች የተገኙ ተጫዋቾች ከተጠባባቂ እየተነሱ እየፈጠሩ የሚገኙት ተፅዕኖ ነው ፤ በቅርብ ዓመታት እንደነ ዓለምብርሃን ይግዛው እና ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ የመሳሰሉ ተጫዋቾች ለዋናው ቡድን ያበቁት ፋሲሎች አሁን ደግሞ እነ ሸምሸዲን መሀመድ እና ናትናኤል ማስረሻ ቀጣዩቹ ኮከቦች ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍንጭ እየሰጡ ይገኛል።

ስልጠናን ከፍ ባለ ደረጃ ሲጀምር የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ረዳት በመሆን በጀመረው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች አሁን ላይ በ33 ነጥቦች በ6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በአስተዳደራዊ ጉዳዩች መነሻነት በብዙ መልኩ በእንከኖች የተሞሉ ጊዜያቶችን ያሳለፈው ቡድኑ ከእነ ችግሮቹ እያሳየ ያለው ተፎካካሪነት አድናቆች የሚቸረው ሲሆን በተለይ ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሰሉ ቡድኖችን አሸንፎ ወደ ነገው ጨዋታ የመምጣቱ ጉዳይ ለፋሲል ከነማ ብርቱ ተፋላሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቋሚ ነው።

በፋሲል ከነማ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ላይ ከሚገኙት አማኑኤል ገብረሚካኤል እና አፍቅሮተ ሰለሞን በተጨማሪ ሀቢብ መሐመድ በቅጣት እንዲሁም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በጉዳት የነገው ጨዋታ የሚያመልጣቸው ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል አድናን ረሻድ ከቅጣት ሲመለስ ቦና ዓሊ በጉዳት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ባደረጓቸው አስራ አራት የእርስ በርስ ግንኙነቶች ፋሲል ከነማዎች አምስቱን በመርታት የበላይነት ሲይዙ አዳማዎች በአንፃሩ አራት ጨዋታዎችን አሸንፈው የተቀሩት ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ።