ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና 13ኛ የአቻ ውጤቱን አስመዝግቧል

40 ጥፋቶች በተሠሩበት ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ እና ነብሮቹ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር ባህር ዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ሲገናኙ የጣና ሞገዶቹ በ21ኛው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 1-1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ቅጣት ላይ በሚገኙት ሀብታሙ ታደሰ እና የአብሥራ ተስፋዬ እንዲሁም በግል ጉዳይ ከቡድኑ ጋር ባልተገኘው ያሬድ ባዬህ ምትክ ፍጹም ፍትሕዓለው ፣ ዓባይነህ ፊኖ እና ፍጹም ጥላሁን ገብተዋል። ነብሮቹ በአንጻሩ በሲዳማ ቡና 2ለ1 ከተሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሄኖክ አርፊጮ ፣ ዳግም ንጉሤ ፣ እንዳለ ዓባይነህ እና ተመስገን ብርሃኑ ወጥተው ቃለአብ ውብሸት ፣ ካሌብ በየነ ፣ በየነ ባንጃ እና ኡመድ ኡኩሪ በቋሚ አሰላለፍ ተካተዋል።


ምሽት 1 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ  የመጀመሪያው ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ 8ኛው ደቂቃ ላይ በሀዲያ ሆሳዕናዎች አማካኝነት ተደርጎ ሳሙኤል ዮሐንስ ለዳዋ ሆቴሳ ለማቀበል የሞከረውን ኳስ የመሃል ተከላካዩ ፍጹም ፍትሕዓለው በግሩም ሁኔታ አቋርጦበታል።

ጨዋታው 13ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የጣና ሞገዶቹ ጨዋታውን ለመምራት የሚችሉበት ወርቃማ ዕድል አግኝተው ነበር። ቸርነት ጉግሳ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ሊጠቀምበት ሲል በረከት ወልደዮሐንስ ጥፋት ሠርቶበታል በሚል በሁለተኛው ረዳት ዳኛ ሲራጅ ኑርበገን ጠቋሚነት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ቸርነት ጉግሳ መትቶት ግብ ጠባቂውን በተቃራኒ አቅጣጫ ቢጥለውም ዒላማውን ሳይጠብቀው ቀርቶ አባክኖታል።

ረዘም ላሉ ደቂቃዎች መሃል ሜዳው ላይ በተጠጋጋ አጨዋወት ያሳለፉት ሁለቱ ቡድኖች ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ግን 23ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያው ካሌብ በየነ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረው ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

የፊት መስመር አጥቂያቸውን ሙጅብ ቃሲምን በጉዳት ምክንያት በፍቅረሚካኤል ዓለሙ ለመተካት የተገደዱት ባህር ዳሮች 38ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ወልደዮሐንስ እና በየነ ባንጃ ጥምረት ሙከራ ቢደረግባቸውም 43ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረው ፍራኦል መንግሥቱ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ በቀኝ እግሩ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል የጣና ሞገዶቹ 49ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ አጋጣሚ አግኝተው መሳይ አገኘሁ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ሊጠቀምበት ሲል ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስ በግሩም ቦታ አያያዝ አግዶበታል።


በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አካላዊ ጉሽሚያዎች በርካታ ጊዜ የኳስ ፍሰቱ በዋና ዳኛው ፊሽካ ሲቆራረጥ በነበረው ጨዋታ በባህር ዳር በኩል 60ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ እና 67ኛው ደቂቃ ላይ በሀዲያ በኩል ተቀይሮ የገባው እንዳለ ዓባይነህ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ከመለሰው ኳስ ውጪ ተጨማሪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳንመለከት ቀርተናል።

ይበልጥ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ በጣና ሞገዶቹ በኩል 78ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር ከያዘው ኳስ ውጪ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠናክረው ለመድረስ ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም 82ኛው ደቂቃ ላይ የባህር ዳር ከተማው ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዶ በጉዳት ምክንያት በአላዛር ማርቆስ ለመቀየር ተገዷል። ጨዋታውም 0-0 ተጠናቋል። የአቻ ውጤቱም ለሀዲያ ሆሳዕና በውድድር ዓመቱ 13ኛ የአቻ ውጤት ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንደነበሩ በሁለተኛው አጋማሽ ግን የጠበቁትን ያህል እንዳላገኙት ሲናገሩ የተሳተላቸው የፍጹም ቅጣት ምት የተጋጣሚያቸውን ጫና እንደቀነሰላቸው በመጠቆም ለ13ኛ ጊዜ ያስመዘገቡት የአቻ ውጤት ጎል በማግባት ችግራቸው ምክንያት ንደመጣ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የባህር ዳር ከተማው ምክትል አሰልጣኝ መብራቱ ሀብቱ በበኩላቸው ጨዋታው በፈለጉት መንገድ እንዳልሄደ በመግለጽ ያመከኑት የፍጹም ቅጣት ምት ውጤት ቀያሪ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ይዘውት የገቡትን አቀራረብ በተጫዋቾች ጉዳት ምክንያት ለመቀየር እንደተገደዱም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።