ሪፖርት | የፋሲል እና አዳማ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

የምሽቱ የፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከሀምበሪቾ ጋር በ21ኛው የሊጉ ሳምንት ነጥብ በተጋራበት ወቅት ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በለውጡም ሳማኪ ሚካኤል ፣ ሐቢብ መሐመድ ፣ ይሁን እንዳሻው ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና በዛሬው ጨዋታ በቋሚነት ተካቶ ድንገተኛ ህመም ባስተናገደው ምኞት ደበበ ቦታ ዮሐንስ ደርሶ ፣ መናፍ ዐወል ፣ እዮብ ማቲያስ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ዓለምብርሀን ይግዛው እና አምሳሉ ጥላሁን ሲተኩ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ላይ ድልን አሳክተው የነበሩት አዳማ ከተማዎች ጉዳት በገጠመው ቦና ዓሊ ምትክ አሸናፊ ኤልያስን በብቸኝነት ያደረጉት ቅያሪ ሆኗል።

ወደ ስልጠናው ዓለም ብቅ እንዲሉ ላደረጓቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የአዳማ ከተማ አቻቸው ይታገሱ እንዳለ በስጦታ ካመሰገኗቸው በኋላ በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ አጋፋሪነት የምሽቱ ጨዋታ ምቾት የሚሰጡ የሜዳ ላይ ቅብብሎችን እያስመለከተን ቢቀጥልም ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች በመመልከቱ ረገድ ግን ዕድለኛ አልነበርም። ከራስ ሜዳ በሚደረጉ ንክኪዎች በቀላሉ ወደ ግብ ክልል የሚደርሱት አዳማ ከተማዎች 7ኛው ደቂቃ ቢኒያም ዐይተን ከርቀት ካደረጋት ዒላማዋን ባልጠበቀች ሙከራ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።

ቀጣዮቹን የጨዋታ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ አዳማዎች ቢኖራቸውም የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ግን በእጅጉ ተቸግረው ቆይተው የኋሊዮሽ ቅብብልን አብዝተው ይጠቀሙ የነበሩት ፋሲሎች 13ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ ለማቀበል ሞክሮ የተሳሳታትን ኳስ መስዑድ አግኝቶ በግራ ለነበረው አቡበከር ሻሚል አመቻችቶለት አማካዩ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቶ ዮሐንስ ራሱ ያበላሻትን ኳስ ተቆጣጥሯታል።

አስራ ሰባት ያህል ደቂቃዎችን ጥንቃቄ መርጠው በመንቀሳቀስ ቆይታ የነበራቸው አፄዎቹ አዳማ ከተማዎች ወደ ፊት ለማጥቃት በሚሳቡበት ወቅት ትተውት የሚሄዱትን ክፍት ቦታ ፈጠን ባሉ ሽግግሮች መነሻቸውን ከመስመር አድርገው በተጫወቱበት ወቅት 18ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ ተከላካዮች መሐል ለመሐል ጃቢር ሙሉ አሾልኮ የሰጠውን ጌታነህ ከበደ ቢያገኛትም የሰይድ ሀብታሙ ቀድሞ መውጣት ኳሷ ወደ ውጪ እንድትወጣ አስችሏታል። አዳማ ከተማዎች ካደረጓት ዒላማዋን ከጠበቀች ብቸኛ ሙከራ ውጪ ከእንቅስቃሴዎች በስተቀር ዕድሎች እምብዛም ያላስተዋልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ጎል ተገባዷል።

ከዕረፍት ተመልሶ በቀጠለው ጨዋታ ፋሲሎች ፈጣን አጀማመርን ባደረጉበት ቅፅበት ጌታነህ ባደረጋት ሙከራ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። ቶሎ ቶሎ በሚጣሉ እና ከቆሙ ኳሶችም ጭምር ጨዋታውን የተቆጣጠሩት አፄዎቹ አምሳሉ ጥላሁን በተከታታይ ባደረጋቸው ጠጣር ቅጣት ምቶች የአዳማን የግብ ክልል መፈተሽ ቢችሉም ከአጠቃቀም አንፃር ደካሞች ነበሩ። 60ኛው ደቂቃ የአዳማው ተከላካይ ፍቅሩ ዓለማየሁ በማቀበል ወቅት አቅጣጫ የቀየረችን ኳስ ዓለምብርሀን በአግባቡ ይዞ የሰጠውን ጌታነህ ሞክሮ የግቡ ቋሚ ብረትን ታካ ኳሷ ወጥታለች።

በንፅፅር በአጋማሹ ተዳክመው የቀረቡትን እና ከኋላ ኳስን ሲጀምሩ ለስህተት ተጋላጭ የነበሩት አዳማ ከተማዎች 66ኛው ደቂቃ መስዑድ እና ቢኒያም ካደረጉት ድንቅ ቅብብል በኋላ መስዑድ በመጨረሻም ለሙሴ ሰጥቶት አጥቂው ቢመታትም ግብ ጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ ኳሷን በጥሩ ብቃት አግዷታል። ይበልጥ እየተቀዛቀዘ የተጓዘው ቀጣየቱ ደቂቃዎች 75ኛው ደቂቃ በአዳማ በኩል ተቀይሮ በገባ በሰከንዶች ውስጥ ጉዳት ያስተናገደው ነቢል ኑሪ በኤልያስ ለገሠ መተካት የቻለ ሲሆን ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ውስጥ 90+3 ላይ ፋሲሎች በእጅጉ ለጎል ቀርበው ነበር። ከግራ በረጅሙ ወደ ሳጥን የተላከን ኳስ ጀሚል በግንባር ገጭቶ ሲመልሳት ተቀይሮ የገባው ብሩክ አማኑኤል ወደ ግብ መቷት ሰይድ ሀብታሙ በድንቅ ብቃት ከመከታት በኋላ ጨዋታው በጎሎች ሳይታጀብ 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መቋጫ በኋላ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ ነገር እንደነበር ገልፀው ከኳስ እና ከኳስ ውጪ ጥሩ መንቀሳቀስ እንደተቻሉ እና ወደ ጎልነት ሊቀየሩ የሚችሉ አጋጣሚዎችን አግኝተው የሚቻለው ሁሉ ቢደረግም ማስቆጠር እንዳልቻሉ እንዲሁም አዳማ ከተማም ጥሩ ቡድን እንደሆነ በንግግራቸው ጠቁመዋል። የአዳማ ከተማ አቻቸው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው በጨዋታው መፈራራቶች እንደነበሩ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴም እንደታየ ከዕረፍት በኋላ ደግሞ የተጋጣሚያቸውን የተወሰኑ ተጫዋቾችን ማርክ እንዳደረጉ ጠቅሰው ውጤቱ መጥፎ አለመሆኑን ተናግረዋል።