ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በመደረግ ሲጀምር ንብ ድል ሲቀናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነገ ጨዋታ ከማድረጉ አስቀድሞ ተከታዩ ኦሮሚያ ፖሊስ ነጥብ በመጣሉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አውቋል።

የሳምንቱ መክፈቻ የሆነው የሀላባ ከተማ እና ንብ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ታይቶበት ያለ ግብ የተጠናቀቀ ሲሆን ከዕረፍት መልስ ግን አምሰት ግቦችን ተመልክተንበታል። በ47ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል ሀላባ ከተማዎች ኳስ ይዘው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ይዘው የገቡትን ከማል አቶም ከፀጋ ከድር ከመስመር በኩል የተሻገረለትን ከመረብ ጋር አገናኝቶ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ጨዋታው ቀጥሎ ጥሩ ፉክክርን እያስመለከተን 57ኛው ደቂቃ ሲደርስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አጥቂው ናትናኤል ሰለሞን የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ይዞ ወደ ሳጥን የገባትን ኳስ በድንቅ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎ ንብን 1-1 እንዲሆኑ አስችሏል። ወደ አቻነት ከተሸጋገረ በኋላ ጨዋታው ግለቱ እየጨመረ ሄዶ ቡድኖቹ መሪ ለመሆን የሚሆጉበትን ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ሲደርስ ተመላክቷል።

73ኛው ደቂቃ ደቂቃ ወሰን ጌታቸው በመስመር በኩል እየገፋ ይዞ የገባትን ኳስ ሲያሻማለት ጀሚል ታምሬ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ሀላባ ከተማን በድጋሚ መሪ ማድረግ ቢችልም መሪነታቸው ግን የቆየው ለሦስት ደቂቃ ብቻ ሆኗል። ግብ በማስቆጠራቸው ከደስታ ድባብ መውጣት የከበዳቸው ሀላባዎች ተከላካዮቻቸው የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ስንታየሁ ሠለሞን በ76ኛው ደቂቃ ንብን አቻ ያደረገች ጎልን አስቆጥሮባቸዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ያህል ደቂቃዎች እየቀሩት በመልሶ ማጥቃት አሸናፊ ለመሆን ኳስን ይዘው ወደ ሀላባ ሳጥን ያመሩት ንቦች 89ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ ዳኛ የተሰጣቸውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ኪዳኔ አሰፋ አስቆጥሮ በመጨረሻም ንብ 3ለ2 በመርታት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ትንቅንቅ አጠናክሮ ቀጥሏል።

10 ሰዓት ሲል ሁለቱን የኦሮሚያ ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ በሁለት አጋማሾች ተከፍሎ ሁለቱም ቡድኖች ጠንካራ ፉክክር አድርገው በአቻ ውጤት ያጠናቀቁበት ነበር። ቀዝቃዛ በነበረው የሀዋሳ ዐየር ውስጥ ሆኖ የተከናወነው ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ኦሮሚያ ፓሊሶች በሽግግር የጨዋታ መንገድ ብልጫውን የያዙ ቢሆንም ከአጨራረስ አኳያ ግን ደካሞች ነበሩ። በተጠቀሰው አጋማሽ ከፍ ባለ ጫና ውስጥ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ኦሮሚያ ፖሊሶች 30ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ በኩል ሳጥኑ ጠርዝ ያገኙትን የቅጣት ምት የአብስራ በለጠ ወደ ጎል አክርሮ ሲመታ ሳሙኤል አሸብር ኳሷን ገጨቶ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል። መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ 45+2 ላይ ፈጠን ባለ መልሶ ማጥቃት ያመሩት ጅማ አባቡናዎች በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መነካቱን ተከተሎ የዕለቱ እንስት ዋና ዳኛ ሲሳይ ራያ የሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት እስጢፋኖስ ተማም ጨዋታወን ወደ 1ለ1 ለውጧል።

ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው መቀጠል የቻለ ሲሆን አባ ቡናዎች ብልጫውን ወስደው በተደጋጋሚ ዕድልን ቢፈጥሩም ጨዋታው ተጨማሪ ጎሎችን ሳያስመለክተን 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል። ይህንን ውጤት ተከትሎ በምድቡ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ላይ የነበረው ኦሮሚያ ፐፖሊስ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ በነገው ዕለት ከይርጋጨፌ ቡና ጋር መሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታውን ሳያደርግ ወደ 2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል።