የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች

ወደ ፍጻሜው የሚያልፈውን ቡድን የሚለየው የግማሽ ፍጻሜ ቀዳሚ ጨዋታ አስመልክተን ያሰናዳናቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ መድን

በፕሪምየር ሊጉ ከስምንት ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጣፋጭ ድል የተቀዳጁት ወላይታ ድቻዎች በሊጉ የጀመሩትን የማንሰራራት ጉዞ ለማስቀጠል እና ወደ ፍጻሜው ለማለፍ ኢትዮጵያ መድንን ይገጥማሉ።

ወላይታ ድቻዎች ቀደም ብለው ባከናወኗቸው ሦስት የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ አስር ግቦች ማስቆጠር ችለዋል። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ዙሮች ላይ በሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ሀድያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሰባት ግቦች ማስቆጠር ቢችሉም ሰሞነኛ የግብ ማስቆጠር ብቃታቸው ግን ደካማ ነው። ቡድኑ ከነገው ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን ጋር ሁለት ግቦች አስቆጥሮ አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም የድክመቱ አንድ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም በውድድሩ አራት ግቦች ያስቆጠረው አጥቂው ቢኒያም ፍቅሩ ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው።

የጦና ንቦቹ በተለይም በሁለቱ የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎች ያሳዩት የተሻሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው ወደ ጨዋታው እንደመቅረባቸው ቀላል ግምት እንዳይሰጣቸው ቢያስገድድም በፊት መስመር ላይ ያላቸው ደካማ የአፈፃፀም ችግር ከተጋጣሚያቸው ሰሞነኛ አቋም ጋር ተዳምሮ ወደ ፍጻሜው ለማለፍ የሚጠብቃቸውን ፈተና ከባድ ያደርገዋል።

ወላይታ ድቻዎች ከድሉ በፊት ምንም እንኳ በተከታታይ ስምንት መርሐግብሮች ከድል ጋር ቢራራቁም በአንፃራዊነት የተሻለ የኋላ ክፍል ነበራቸው፤ ጥምረቱ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ላይ ካሳየው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ከአንድ ግብ በላይ ያስተናገደው በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው። ይህ የኋላ መስመር ጥንካሬም የጦና ንቦቹ ውጤት ሊወስኑ ከሚችሉት መመዘኛዎች አንዱ ነው። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ቡድኑ ጠንካራውን የኢትዮጵያ መድን የፊት መስመር በተሻለ መንገድ መቆጣጠር ከቻለ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ የመውጣት ዕድሉን ያሰፋለታል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።

ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ ፍጹም ተለውጠው የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች በቅርብ ሳምንታት በፕሪምየር ሊጉ ያስመዘገቡት ጥሩ ውጤት በነገው
ጨዋታ ቀላል ግምት እንዳይሰጣቸው ያደርጋል።

መድኖች በፕሪምየር ሊጉ ከ12 ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ ሁለት ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ችለዋል። ቡድኑ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች ተላቅቆ ወደ አሸናፊነት መንገድ ከመመለሱም በተጨማሪ ድሎቹ በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጠው መቻል እና በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር እና ሽንፈት ሳይቀምስ ከዘለቀው ወልቂጤ ከተማ ላይ የተመዘገቡ መሆናቸው ቡድኑ ምን ያህል እንደተሻሻለ ማሳያዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ መድኖች ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ማስቆጠር ቢችሉም የከዚህ ቀደም የግብ ማስቆጠር ብቃታቸው ደካማ ነበር። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ቡድኑ አስፈሪ የፊት መስመር ጥምረት መገንባት ችሏል፤ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ዘጠኝ ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመርም ለቡድኑ መሻሻል የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። መድኖች በተከታታይ ሦስት መርሐግብሮች ላይ በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው በመጨረዎቹ ጨዋታዎች ላይ መሻሻሎች አሳይቷል። የኋላ ክፍሉ ሲዳማ ቡና፣ መቻል እና ወልቂጤ ከተማን በገጠመባቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ ለቡድኑ ውጤት ማማር የበኩሉን ቢወጣም በነገው ዕለት የሚጠብቀውን ፈተና ቀላል አይሆንም። ወላይታ ድቻዎች ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት ከቡድን እንቅስቅሴ በዘለለ ደካማ የሚባል አፈጻጻም ያለው የፊት መስመር ቢይዙም በውድድሩ በሦስት ጨዋታዎች አስር ግቦች ማስቆጠራቸው መዘንጋት የለበትም።

የሁለቱም ቡድኖች የውድድሩ ጉዞ

ድሬዳዋ ከተማ 1 – 2 ኢትዮጵያ መድን

ዳዊት እስጢፋኖስ   ቹኩዌሜካ ጎድሰን
ያሬድ ዳርዛ

አርሲ ነገሌ 1 – 2 ኢትዮጵያ  መድን

ታምራት ኢያሱ    በርናንድ ኦቼንግ
ቹኩዌሜካ ጎድሰን

አዳማ ከተማ 1 – 3 ኢትዮጵያ መድን

አሸናፊ ኤልያስ   አሚር ሙደሲር
ወገኔ ገዛኸኝ
ያሬድ ዳርዛ

ወላይታ ድቻ 3-1 ደሴ ከተማ

ቢኒያም ፍቅሩ    ሙሉጌታ ካሳሁን
ፀጋዬ ብርሀኑ
ዮናታን ኤልያስ

ሀድያ ሆሳዕና 2 – 5 ወላይታ ድቻ

መለሰ ሚሻሞ(2)    ቢንያም ፍቅሩ(2)
አብነት ደምሴ
ዮናታን ኤልያስ
ዘላለም አባተ

ቅዱስ ጊዮርጊስ 1 – 2 ወላይታ ድቻ

ታምራት ኢያሱ       ቢንያም ፍቅሩ
ብሥራት በቀለ