የ22ኛ ሳምንት የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ተላልፈዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ያሳለፍነውን የጨዋታ ሳምንት መነሻ በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በድሬዳዋ ከተማ የነበረውን ቆይታ አገባድዶ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ሀዋሳ ያመራል። ሆኖም በመጨረሻው የድሬዳዋ ሳምንት ጨዋታዎች ተጥሰዋል በተባሉ የዲሲፕሊን መርሆች የውድድር እና ሥነስርዓት ኮሚቴ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ታውቋል።

ጠንከር ያለ ቅጣት ከተላለፈባቸው መካከል የሻሸመኔ ከተማው የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አጥናፉ ታደሰ ዳኛን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ሲሆን የቡድን አመራሩ ለፈፀሙት ጥፋት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገዱ እና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 10000 /አስር ሺ/ እንዲከፍሉ ፣ በ19ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ፋሪስ አለዊ(ወልቂጤ ከተማ) ዳኛን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ሲሆን ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድ እና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሦስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል።

– የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች ሞሰስ ኦዶ የውሃ ፕላስቲክ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች መቀመጫ ስለመወርወሩ እና አፀያፊ ስድብ ስለመሳደቡ ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን ተጫዋቹ የውሃ ፕላስቲክ በመወርወሩ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 25 000 /ሃያ አምስት ሺህ /እንዲሁም አፀያፊ ስድብ በመሳደቡ 3/ሶስት ጨዋታ እንዲታገድና ብር 3000 /ሦስት ሺህ / እንዲከፍል ፤

– የወላይታ ድቻ ምክትል አሰልጣኝ ግዛቸው ጌታቸው የተጋጣሚን ቡድን ተጫዋች አጸያፊ ስድብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ቀርቦባቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ  መሠረት 6 /ስድስት/ ጨዋታ እንዲታገዱ እና ብር 5000 /አምስት ሺህ/ እንዲከፍሉ እንዲሁም ጊት ጋትኩት(ሲዳማ ቡና) 10 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 2 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 2000 /ሁለት ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል።