የሲዳማ ቡና የዕግድ ውሳኔ ፀንቷል

ሲዳማ ቡና በግራ መስመር ተከላካዩ ለቀረበበት ክስ የጠየቀው ይግባኝ ውድቅ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊው ሲዳማ ቡና የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው መሐሪ መናን ከክለቡ ማሰናበቱ ይታወሳል። ተጫዋቹም በክለቡ እስከ ያዝነው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ውል እያለኝ ምንም ክፍያን ሳላገኝ ከክለቡ አልለያይም በማለት ቅሬታውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በማቅረብ ያለፉትን ወራቶች ጉዳዩ በተደጋጋሚ ሲታይ ቆይቷል።

የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ክለቡ ምላሽ እንዲሰጠኝ ጠይቄ ምላሽ አላገኘሁ ስለሆነም ክለቡ ለተጫዋቹ በወር 378ሺህ ብር ከሐምሌ 1 እስከ የካቲት 30 _ 2016 ድረስ በአንድ ጊዜ ክፍያ በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲፈፅም ካልሆነ ግን ክለቡ ከፌዴሬሽኑ ምንም አይነት አገልግሎት እና የተጫዋች ዝውውር እንዳይፈፅም በማለት ውሳኔን መስጠቱ ይታወሳል። ክለቡ የተወሰነበት ውሳኔ ልክ አለመሆኑን በመግለፅ ለፌዴሬሽኑ አቤቱታውን ያቀረበ ቢሆንም የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ በመጨረሻም የክለቡን ቅሬታ ውድቅ በማድረግ ለተጫዋቹ ቀድሞው የተሰጠው ውሳኔን በማፅናት ጉዳዩ መቋጨቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኛችሁ መረጃ ይጠቁማል።