በኢትዮጵያዊቷ እንስት ባለሙያ ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቋል

በላይቤሪያ ለሚገኙ ኢንስትራክተሮች በኢትዮጵያዊቷ የካፍ ኢንስትራክተር ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ፍፃሜውን አግኝቷል።

በላይቤሪያ እግርኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት በሀገሪቱ ለሚገኙ የካፍ ኢንስትራክተሮች በኢትዮጵያዊቷ ዕንስት የካፍ ኢንስትራክተር መሪነት ሲሰጥ የነበረው የሪፍሬሽመንት ኮርስ ሥልጠና በትናንትናው ዕለት ተቋጭቷል። የላይቤሪያን የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝ እየመራች የምትገኘዋ ኢትዮጵያዊቷ የካፍ ኢንስትራክተር ሠላም ዘርዓይ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለካፍ ባሳወቀው ጥሪ መሠረት ሥልጠናውን እንድትሰጥ የተደረገ ሲሆን ሥልጠናው በክፍል እና በተግባር ለሦስት ተከታታይ ቀናቶች ያህል በዋና ከተማዋ ሞንሮቪያ ተሰጥቶ ትናንት አመሻሹን ተቋጭቷል።

በሥልጠና መርሀግብሩ ላይ የላይቬሪያ ዜግነት ያላቸው አስራ ሁለት የካፍ ኢንትስትራክተሮች ተካፋይ መሆን የቻሉ ሲሆን በቀጣዮቹ ወራትም ተመሳሳይ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እንደሚኖሩም የእግር ኳስ ፌድሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ራጂ ተናግረዋል።