የትግራይ ክልል ክለቦች ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሊግ ከ2017 ጀምሮ ተመልሰው እንዲወዳደሩ ውሳኔ ተላለፈ

የትግራይ ክልል ክለቦች ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሊግ ከ2017 ጀምሮ ተመልሰው እንዲወዳደሩ ውሳኔ መተላለፉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ

ፌዴሬሽኑ ይፋ ያደረገው ውሳኔ የሚከተለውን ይመስላል፦

የኢፌዴሪ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የክልሉ ክለቦች በፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ሲያደርጓቸው የነበሩ ውድድሮችን ማቋረጣቸውን በመጥቀስ መንግሥት እና የትግራይ ክልል አመራሮች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በመፈረም ሁሉም ነገር ወደነበረበት እንዲመለስ መግባባት ላይ በተደረሰው መሠረት ሁሉም የትግራይ ክልል ክለቦች ከጦርነቱ በፊት ሲወዳደሩበት ወደነበረው ሊግ ከ2017 ጀምሮ ተመልሰው እንዲወዳደሩ በላከው ደብዳቤ ጠይቋል።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ የትግራይ ክልል ክለቦች ከሁለት ዓመት በላይ በውድድር ላይ ያልተሳተፉ በመሆኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደርያ ደንብ መሠረት ሙሉ ለሙሉ ከውድድር ከመሰረዝ ይልቅ አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው ውድድር እንዲጀምሩ ከዚህ ቀደም አስተላልፎት የነበረውን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ በመሻር የትግራይ ክልል ክለቦች ከጦርነቱ በፊት ሲወዳደሩበት ወደነበረው ሊግ ከ2017 ጀምሮ ተመልሰው እንዲወዳደሩ ከመንግሥት የቀረበውን አቅጣጫ በመቀበል ውሳኔ አሳልፏል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አ/ማ በተላከው ደብዳቤም ሊጉ በ2017 የወድድር ዘመን በ19 ቡድኖች መካከል ተደርጎ 5 ቡድኖች ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲወርዱ በማድረግ በ2018 ከዚህ ቀደም ወደነበነረበት 16 ክለቦች እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀምጧል። የከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ውድድሮች በተመሳሳይ ተግባራዊ እንዲደረጉ አቅጣጫ ተሰጥቷል።