ሪፖርት | አባካኝነት ሻሸመኔ ከተማን ዋጋ አስከፍሏል

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ነቢል ኑሪ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ አዳማ ከተማ ከሻሸመኔ ከተማ ላይ ወሳኝ ድል እንዲቀዳጁ አስችላለች።

አዳማ ከተማዎች በመጨረሻ ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ባደረጓቸው ሶስት ለውጦች ፍቅሩ ዓለማየሁ ፣ አሸናፊ ኤልያስ እና ዮሴፍ ታረቀኝን አስወጥተው በምትካቸው ሬድዋን ሸሪፍ ፣ አድናን ረሻድ እና ቦና ዓሊን ያስገቡ ሲሆን ሻሸመኔ ከተማዎች በአንፃሩ በድሬዳዋ ከተማ ከተረታው ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም የዓብስራ ሙሉጌታ ፣ አሸብር ውሮ ፣ ምንተስኖት ከበደ ፣ ሄኖክ ድልቢ እና አብዱልከሪም ቃሲም ወጥተው በምትካቸው ወጋየሁ ቡርቃ ፣ ኢቢሳ ከድር ፣ ገዛኸኝ ደሳለኝ ፣ ስንታየሁ መንግስቱ እና ሁዛፍ ዓሊን በመተካት ወደ ዛሬ ጨዋታ ቀርበዋል።

የሊጉን የሀዋሳ ከተማ የአምስት የጨዋታ ሳምንታት ቆይታ መክፈቻ የነበረውን ይህን መርሃግብር የሲዳማ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ እና የአክሲዮን ማህበሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር ጅማሮውን አድርጓል።

በአልቢትር ተፈሪ አለባቸው የማብሰርያ ፊሽካ ጅማሮውን ያደረገው ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት የተሻለን አጀማመር ያደረጉበት ነበር ፤ በፈጣን ጥቃቶች ጨዋታውን የጀመሩት ሻሸመኔዎች በ11ኛው ደቂቃ ወጋየሁ ቡርቃ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ስንታየሁ መንግስቱ ወደ ግብ የሞክራት እና ሰዒድ ሀብታሙ በመለሳት ኳስ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

በሂደት የተወሰደባቸውን ብልጫ የቀለበሱ የሚመስሉት አዳማ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ድርሻቸውን በማሳደግ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ ቢሆንም ሙሴ ኪሮስ በ17ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ሞክሮ በግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣችበት ኳስ ውጭ ዕድሎችን መፍጠር ረገድ ግን ፍፁም ደካማ ነበሩ።

በአንፃሩ መልሶ ማጥቃት ተደጋጋሚ ስጋቶችን አዳማ ላይ ሲደቅኑ የነበሩት ሻሸመኔ ከተማዎች በ22ኛው ደቂቃ በፕሪምየር ሊግ በሻሸመኔ ከተማ መለያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ሁዛፍ ዓሊ ከቀኝ መስመር አመቻችቶ የሰጠውን አስደናቂ ኳስ ስንታየሁ መንግስቱ ያመከናት እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ እዮብ ገ/ማርያም ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ያደረጋት ሙከራ ተጠቃሽ የአጋማሹ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ሁለቱም ቡድኖች በጋራ አምስት ተጫዋቾችን ለውጠው በጀመሩት የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የውጤት ለውጥ ያስመለከተን ገና በማለዳ ነበር ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ወጣቱ አጥቂ ነቢል ኑሪ በ49ኛው ደቂቃ በሳጥን ጠርዝ ያገኘውን ኳስ ተቆጣጥሮ በግሩም አጨራረስ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት መታተር የጀመሩት ሻሸመኔ ከተማዎች ከመስመር በሚጣሉ ኳሶች በተደጋጋሚ ወደ የአዳማ ሳጥን ቢጎበኙም ጥረታቸው ግን ፍሬያማ አልነበረም ፤ በተለይም በ66ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን የተሻገለትን ኳስ ስንታየሁ መንግሦቱ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ያመከናት ኳስ እንዲሁም በ86ኛው ደቂቃ ስንታየሁ መንግሦቱ ያሾለከለትን ኳስ እዮብ ገ/ማርያም አስቆጠራት ተብሎ ሲጠበቅ ሱራፌል ዓወል ተንሸራቶ ያዳነበት ኳስ በጣም አስቆጭ ሙከራዎች ነበሩ።

ምንም እንኳን ግብ ካስቆጠረ በኃላ በአመዛኙ ብልጫ የተወሰደባቸው አዳማ ከተማዎች ይበልጥ አጋማሹን በጥንቃቄ በመጫወት ያገባደዱ ሲሆን የሻሸመኔ ከተማዎች ጥረት ግብ ሳያስገኝላቸው ጨዋታው በአዳማ ከተማ የ1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ከለመድነው ሰዓት ውጭ የተደረገ ጨዋታ በመሆኑ በተወሰነ መልኩ ልጆቻቸው ላይ ጫና መፍጠሩን አንስተው የመጫወቻ ሜዳ መለወጡ በራሱ በተወሰነ መልኩ ጨዋታውን እንዳከበደባቸው ሲገልፁ በአዳማ ከተማ ታሪክ የተሻለውን የነጥብ ብዛት ይዘው ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ገልፀዋል ፤ በአንፃሩ የሻሸመኔ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው ተጫዋቾቻቸው ቡድኑ በተበተነበት ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲሰሩ ስለመቆየታቸው ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልፀው ተጫዋቾች ይበልጥ የሙያተኝነት እሳቤን መላበስ እንዳለባቸው ሲያሳስቡ ስንታየሁ መንግሦቱ በዚህ ልክ ዕድሎችን በማምከኑ ራሱን መጠየቅ አለበትም ሲል ተናግረዋል።