ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን በድል ጉዞው ቀጥሏል

የ26ኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን የምሽት ጨዋታ የተለያዩ የሜዳ ላይ ክስተቶችን አስተናግዶ ኢትዮጵያ መድኖች ተከታታይ ስድስተኛ ድላቸውን ሲያሳኩ አዳማ ከተማዎች እጅ ለመስጠት ተገደዋል።

ኢትዮጵያ መድን አምስት ጎል አስቆጥሮ ድሬደዋ ከተማን ካሸነፉበት ቡድናቸው ስብስብ ውስጥ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በርናንድ ኦቼንግ እና መሐመድ አበራን በማሳረፍ በሰዒድ ሀሰን እና አቡበከር ሳኒ ቀይረው ወደ ሜዳ ሲገቡ። እንዲሁ አዳማ ከተማዎች ሲዳማ ቡናን ከረቱበት ስብስባቸው በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ ግብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ፣ አህመድ ረሺድ እና ነቢል ኑሪን ምትክ በግብ ጠባቂ በቃሉ አዱኛ፣ በታዬ ጋሻው እና ዮሴፍ ታረቀኝን ተጠቅመው ወደ ሜዳ ለማስገባት ቢያስቡም ፍቅሩ አለማየሁ በልምምድ ላይ ድንገተኛ ህመም በማጋጠሙ ሳይታሰብ ሱራፌል ዐወል ተክቶት ገብቷል።

ፌደራል ዳኛ መለሰ ንጉሴ ለስድስተኛ ጊዜ በመሩት በዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ሁለቱም ቡድኖች ከመጡበት የመጨረሻ ጨዋታ ድል እና ከሚከተሉት የጨዋታ እንቅስቃሴ አንፃር በጎል የታጀበ አዝናኝ እንቅስቃሴ እንደሚያስመለክተን የተገመተ ቢሆንም በመጀመርያው አጋማሽ የታሰበውን ነገር መመልከት አልቻልንም። ይህም ሆኖ ቡድኖቹ ከራሳቸው ሜዳ በመነሳት በፍጥነት በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ ወደ ፊት በመሄድ የሚያደርጉት መልካም ምልልሶችን ቢያስመለክተንም ጨዋታው ሙከራዎች ይጎሉት ነበር።

ከአዳማዎች በተሻለ መድኖች ኳሱን ተቆጣጥረው በጥሩ ቅብብሎሽ በተደጋጋሚ የማጥቃት ዞን ቢደርሱም ሙከራዎችን በመፍጠር በኩል ተቸግረው ታይተዋል። አዳማዎች በበኩላቸው እነርሱ ሜዳ የመጣውን ኳስ ነጥቀው በፍጥነት በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ቢያስቡም በተመሳሳይ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በደካማ ውሳኔ ኳሶቻቸው ይበላሹ ነበር።

ጨዋታው በሁለቱም በኩል በነበሩ ጠንካራ መከላከሎች እንዳለ ሆኖ በተመሳሳይ መንገድ በሚደረግ እንቅስቃሴዎች ቀጥሎ በ45ኛው ደቂቃ በአዳማ በኩል ቻርለስ ሪቫኑ ከሳጥን ውጭ ብዙም ጉልበት ያልነበረው ለጎል የቀረበ ሙከራ ከተደረገ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ዮሴፍ ታረቀኝ ከግራ መስመር ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ የመታውን ግብ ጠባቂው አቡበከር ያዳነበት በጨዋታው የመጨረሻ ሁለት ሙከራዎችን ካስመለከተን ውጭ ሌለ ተጠቃሽ የጎል ሙከራ ሳንመለከትበት የጨዋታው አጋማሽ ወደ መጠናቀቂያ ላይ ደርሷል።


ከዕረፍት መልስ በከፍተኛ ዝናብ ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በኩል በማጥቃት ረገድ የነበረባቸውን አቅም በማሳደግ ወደ ሜዳ ሲገቡ በ59ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ ከርቀት በጥሩ መንገድ የተመጠነ ኳስ ሚሊዮን ሰለሞን የላከውን አብዱልከሪም መሐመድ ሳጥን ውስጥ ተቆጣጥሮት የመታውን ለጥቂት በግቡ ቋሚ ተኳ ከወጣው የመድኖች ሙከራ በኋላ ጨዋታው ከፍተኛ መነቃቃት አሳይቷል።

በተሻለ ሁኔታ ይንቀሳቀሱ የነበሩት መድኖች በ63ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ጎል አግኝተዋል። አቡበከር ሳኒ በፍጥነት ኳስ ይዞ ወደፊት ለመሄድ በሚያደርገው ጥረት ሱራፌል ዐወል የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ሐይደር ሸረፋ በግሩም ሁኔታ ቦታ አይቶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ከጎሉ በኋላ የጨዋታው እንቅስቃሴ ከፍ ባለ ግለት ይቀጥላል ቢባልም 68ኛው ደቂቃ በስታዲየሙ ቀኝ ክፍል በኩል ያለው የስታዲየሙ ፓውዛ መብራት መጥፋቱን ተከትሎ ጨዋታው ለደቂቃዎች ለመቋረጥ ቢገደድም የመብራቱ ሁኔታ ሳይስተካከል የጨዋታውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ቡድኖቹ በመፍቀዳቸው ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሏል።

ምላሽ በመስጠት በፍጥነት ወደ ጨዋታው ለመግባት ያሰቡት አዳማዎች 69ኛው በህመም ምክንያት ከመጀመርያው አስተላለፍ የወጣው ተከላካዮ ፍቅሩ አለማየሁ ተቀይሮ በመግባት ካደረገው ጠንካራ ሙከራ በኋላ በድጋሚ
74ኛው ደቂቃ ቻርለስ ሪቫኑ ከሳጥን ውጭ በጠንካራ ምት ወደ ጎል የመታውን ግብ ጠባቂው አበቡበከር ሲመልሰው ተቀይሮ የገባው ነቢል ኑሪ ነፃ የጎል ዕድል አግኝቶ በሚያስቆጭ ሁኔታ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ አዳማዎችን ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

የጨዋታው ግለት ቀጥሎ በ76ኛው ደቂቃ አዳማዎች የተቀጡበትን ሁለተኛ ጎል ሊያስተናግዱ ችለዋል። አብዱልከሪም መሐመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ከተከላካይ ጀርባ የነበረው አለን ካይዋ በጥሩ አጨራረስ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስገኝቷል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ የመድኖችን የጎል መጠን ከፍ ሦስት ከፍ ያደረገች ጎል አግኝተዋል። አቡበከር ሳኒ በተከላካዮች መሐል በድንቅ ሰንጣቂ ኳስ ያቀበለውን አብዲሳ ጀማል ኳሱን በተገቢው ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ፊት በመሄድ የመድኖችን ጎል አስቆጥሯል።

80ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ታረቀኝ ከቅጣት ምት የመታውን ጀሚል ያቆብ አግኝቶ ለአዳማ ጎል ቢያስቆጥርም ብዙም ሳይቆይ ኢትዮጵያ መድኖች የአዳማን ወደ ጨዋታው የመግባት ተስፋ ያጨለመች ጎል በ86ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በግንባሩ በመግጨት ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስገኝቶ ጨዋታው በኢትዮጵያ መድኖች 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።