ሪፖርት | ቡናማዎቹ የኢትዮጵያ መድንን የተከታታይ የሰባት ጨዋታ የድል ጉዞን ገተውታል

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ አምስተኛ ድሉን በማሳካት ደረጃውን ሲያሻሽል ኢትዮጵያ መድኖች ከሰባት ተከታታይ የድል ጉዞ በኋላ ሽንፈት አስተናግደዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች ሻሸመኔ ከተማን 2ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በርናርድ ኦቼንግ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ብሩክ ሙሉጌታ እና አለን ካይዋ ወጥተው ሰዒድ ሀሰን ፣ አሚር ሙደሲር ፣ መሐመድ አበራ እና ጄሮም ፊሊፕ ተተክተዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንጻሩ ወልቂጤ ከተማን 4ለ0 ከረቱበት አሰላለፍ ባደረጉት የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ በፍቃዱ ዓለማየሁ ፣ ራምኬል ጀምስ ፣ ዋሳዋ ጄኦፍሪ ፣ ሬድዋን ናስር ፣ ስንታየሁ ወለጬ እኔ ጫላ ተሺታ ወጥተው ወንድሜነህ ደረጄ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ ይታገሱ ታሪኩ ፣ አብደልከሪም ወርቁ እና አንተነህ ተፈራ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካትተዋል።

9 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ ፉክክር በተደረገባቸው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች በኢትዮጵያ ቡና በኩል አንተነህ ተፈራ 2ኛው ደቂቃ ላይ ከይታገሱ ታሪኩ 14ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከአብዱልከሪም ወርቁ በቀኝ መስመር ከተገኙ የቅጣት ምቶች በተሻገሩለት ኳሶች በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ሞክሮ የመጀመሪያውን ሳያገኘው ሲቀር ሁለተኛውን ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶበታል። በአንጻሩ ኢትዮጵያ መድኖች 20ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ ከአቡበከር ሳኒ ተመቻችቶለት ካደረገው ፈታኝ ያልሆነ ሙከራ ውጪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

የሚቆራረጡ እና የማያድጉ ንኪኪዎችን እያስመለከተን የቀጠለው ጨዋታ በመጨረሻም አንተነህ ተፈራ ከተደጋጋሚ ዒላማቸውን ያልጠበቁ የግንባር ሙከራዎች በኋላ ስኬታማ ሆኖ ለቡናማዎቹ ጎል አስገኝቷል። 32ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው ቀኝ ክፍል አማኑኤል አድማሱ ያሻገረለትን አንተነህ ተፈራ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።

ከጎሉ በኋላ ነጨዋታው ግለት ከፍ ባለ ደረጃ ተቀይሮ ወደ ፊት የሚደረጉ ምልልሶችን አስመልክቶናል። በዚህ ሂደት በ35ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ መድኖች በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ አብዱልከሪም መሐመድ በጥሩ ሁኔታ ያመቻቸው እና ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ጎል የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን በረከትን ቢያልፈውም ወልደአማኑኤል ጌቱ በአስደናቂ የመከላከል ብቃት ኳሱ ጎል እንዳይሆን በግንባሩ ወደ ውጭ ያወጣው ለመድኖች ወደ ጨዋታው ለመግባት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ነበር።

አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ ያልሰጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከራሳቸው ሜዳ ክፍል በሚገርም ቅብብሎች አስራት ቱንጆን መነሻ አድርጎ መሐመድኑር ናስር በአንድ ንክኪ ለአብዱልከሪም ወርቁ አቀብሎት አብዱልከሪም ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ከውሳኔ ችግር የተነሳ ያመከነው የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ኢትዮጵያ መድኖች ጄሮም ፊሊፒን በያሬድ ዳርዛ ያደረጉት ፈጣን የተጫዋች ለውጥ ብዙም ጊዜ ሳይወስድ ውጤታማ አድርጓቸዋል። በ47ኛው ደቂቃ ቡናማዎቹ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በሚያደርጉት ቅብብል የተፈጠረውን ስህተት ተጠቅሞ ወገኔ ገዛኸኝ ለያሬድ ዳርዛ አቀብሎት ያሬድ በጥሩ እርጋታ ሳጥን ውስጥ በመግባት ግሩም ጎል በማስቆጠር ቡድኑን አንድ አቻ ማድረግ ችሏል።

ከአቻነቱ ጎል በኋላ ጨዋታው ፈዘዝ ብሎ የቀጠለ ቢሆንም የቡናማዎቹ የ68ኛ ደቂቃ ጎል ጨዋታውን አነቃቅቶታል። አብዱልከሪም ወርቁ በሜዳው ቀኝ ክፍል ሳጥን ውስጥ ገብቶ ወደ ጎል የመታውን እና በጎሉ አግዳሚ የተመለሰውን በስም ሞክሼ የሆነው አብዱልከሪም መሐመድ በራሱ ላይ ጎል አስቆጥሮ ቡናማዎቹ መሪ መሆን ችለዋል።

የተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች
ጫና ለመፍጠር ጥረት አድርገው በ76ኛው ደቂቃ ዮናስ ገረመው ጥሩ ሰንጣቂ ኳስ ለአቡበከር ሳኒ አቀብሎት ሳይጠቀምበት ከቀረው አጋጣሚ በቀር በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል 79ኛው ደቂቃ በቅብብሎች መሃል ብሩክ በየነ ወደ ኋላ አድርጎ ያመቻቸለትን አብዱልከሪም ወርቁ በቀጥታ ወደ ጎል ቢመታውም ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ካዳነው ሙከራ በቀር በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ ነገሮች ሳንመለከት ጨዋታው በቡናማዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከተከታታይ ድላቸው የተገቱት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በአስተያየታቸው የተጫዋቾቻቸው የስነ ልቦና ዝግጅት ጥሩ ተነሳሽነት እንዳልነበረ እና ከሜዳቸው እንዳይወጡ ለማድረግ የሰራነው የታክቲክ ስህተት እኛን ፍርክስክስ አድርጎናል ካሉ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመግባት ጊዜ ቢወስድባቸውም በራሳቸው በተቆጠረ ጎል መሸነፋቸውን ሲናገሩ አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በበኩላቸው ያደረጉት የአምስት ተጫዋች ለውጥ እና ልጆቹ ሜዳ ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ እንዲሁም ቡድኑ ውጤታማ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው በቀጣይ ሳምንት ላለው የደርቢ ጨዋታ በጥሩ መነቃቃት ጨዋታውን ለማድረግ እንደሚያስቡ ጠቁመዋል።