ሪፖርት | ሀምበሪቾ ከሊጉ የወረደ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል

የምሽቱ የሀምበሪቾ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ያለ ጎል ቢጠናቀቅም ሀምበሪቾ ዱራሜ በመጣበት ዓመት ከሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።

በ28ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር ሀምበርቾዎች በ27ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና 2ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አልአዛር አድማሱ እና አብዱልከሪም ዱግዋ ወጥተው ሙና በቀለ እና በኃይሉ ተሻገር ተተክተዋል። የጦና ንቦቹ በአንጻሩ ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ1 ያሸነፉበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል።

በፌድራል ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ በተመራው የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር ብልጫውን መያዝ ቢችሉም እንደነበራቸው ከፍ ያለ ተነሳሽነት ግን ግልፅ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ግን ወረድ ያለ አቀራረብ ነበራቸው። ቡድኑ ከአማካይ ክፍል ኳስን በንክኪ ወደ ሁለቱ ኮሪደሮች በመለጠጥ በጥልቀት ለመጫወት ጥረት ያደርጉ የነበረ ቢሆንም በጥብቅ መከላከል የኋላ መስመራቸውን ጥቅጥቅ ባለ ሽፋን ሰጥተው የሚጫወቱትን የሀምበሪቾ የተከላካይ ክፍልን በመስመሩ ረገድ ፍፁም ተዳክመው ተስተውሏል።

ሜዳ ላይ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በስተቀር በሙከራዎች መድመቅ የተነሳው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ድቻዎች 26ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን መነሻዋን ያደረገች ኳስን ናታን ጋሻው በግንባር ገጭቶ በንክኪ መውጣት የቻለችዋ እና 30ኛው ደቂቃ ናታን የሰጠውን አብነት ደምሴ ተፈጥሯዊ ባልሆነው እግሩ መቶ ወደ ውጪ የወጣበት በጨዋታው የነበሩ ደካማ ዕድሎች ሲሆኑ አጋማሹም እንደነበረው ቀዝቃዛ አቀራረብ ያለ ጎል ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ወላይታ ድቻዎች እዮብ ተስፋዬን በቢኒያም ፍቅሬ በመተካት የአጥቂ ክፍላቸው ላይ ዕድሳት በማድረግ መመለስ ቢችሉም አሁንም በጥብቅ መከላከል የተጠመዱትን የሀምበሪቾን የኋላ ክፍል አልፎ ኳስ እና መረብን ማዋሀዱ ላይ ዕድለኞች አልነበሩም። 47ኛው ደቂቃ ኬኔዲ ከበደ ከርቀት አክርሮ መቶ ምንታምር መለሠ በጥሩ ቅልጥፍና ከመለሳት በኋላ ናታን ጋሻው ወደ ጎልነት ቀይሯት ከጨዋታ ውጪ የተባለችዋ እና አብነት ደምሴ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ አክርሮ መቶ በግቡ ቋሚ ብረት ስር ታካ የወጣችዋ ኳስ የወላይታ ድቻን ከፍ ያለ ጫናን ያሳዩ ጥቃቶች ቢሆኑም ቡድኑ ላይ ግን የስልነት ችግሮች ጎልተው ታይተዋል። አብዛኛውን ደቂቃ መከላከሉ ላይ ተጠምደው ያመሹት እና በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ጥቂት ዕድሎችን ለመጠቀም የሚታትሩት ሀምበሪቾዎች 53ኛው ደቂቃ በተመስገን አሰፋ የርቀት ሙከራን ከውነው የግብ ዘቡ ቢኒያም ገነቱ ይዞበታል።

የመጨረሻዎቹን ሀያ ያህል ደቂቃዎች የማጥቃት ቁጥራቸውን በማሳደግ በድግግሞሽ ጥቃት የሰነዘሩት ድቻዎች 72ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል ኬኔዲ ከበደ ሞክሮ ምንታምር እንደምንም ያዳነበት እና በሌላ አጋጣሚ ፍፁም ወደ ጎል አሻምቶ አብነት በግንባር ገጭቶ በዕለቱ ጥሩ ምሽትን ያሳለፈው ምንታምር ሳይቸገር ይዞበታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ መባቻው ላይ ወላይታ ድቻዎች በናታን ጋሻው እና ቢኒያም ፍቅሬ አማካኝነት ያለቀላቸውን ሁለት አጋጣሚዎች አግኝተው ካመከኗቸው በኋላ ጨዋታው ጎል ሳያስመለክተን 0ለ0 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሀምበሪቾ ዱራሜ በ9 ነጥቦች የሊጉን ግርጌ እንደያዘ ለከርሞ ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ቀድመው እንደጠበቁት ጠንካራ ጨዋታ እንደሆነ እና የተጋጣሚያቸውን መከላከል ሰብረው ለመግባት መቸገራቸውን ጠቅሰው በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ደካማ እንደነበሩ ሳይሸሽጉ ቀጣዮቹን ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ መዘጋጃ እንደሚያደርጓቸው ሀሳባቸውን ሲሰጡ የሀምበርቾው አሰልጣኝ ብሩክ ሲሣይ በበኩላቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ ያሉ ችግሮች እየተንከበላሉ እዚህ እንዳደረሷቸው ጠቁመው ቢወርዱም የሊጉን ደረጃ ላለማውረድ ተጠናክረው መቅረባቸውን ገልጸው ከክፍያ ጋር በተያያዘ ተጫዋቾቹን ከቤታቸው ድረስ ሄደው በተማጽኖ ይዘው ይመጡበት የነበረውን አጋጣሚ አውስተው የሚችሉትን ሁሉ እንደጣሩ እና በቀጣይ ጨዋታዎችም ላለመውረድ ከሚጫወቱ ክለቦች ጋር ሲገናኙ በጀርባ የሚኖሩ ነገሮች እንዳይኖሩ እንደሚፈልጉ ተናግረው ክለቡ ለራሱ ጥቅም ሲል ለተጫዋቾች ደመወዝ መክፈል እንዲችል እና የሀምበርቾ ብዙ ክፍተቶች በተለይም በገንዘብ ጉዳይ ለሌሎች ቡድኖች ትምህርት እንደሚሆኑ ሀሳባቸውን ሰጥተው በፈተናቸው ወቅት ከጎናቸው ላልተለዩ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።