የ8ኛው ሳምንት 8 እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ተካሂደዋል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው አብርሃም ገ/ማርያም መረጃዎችን አገላብጦ ከውጤቶች በስተጀርባ ያሉ እውነታዎችን እንዲህ አሰናድቷቸዋል፡፡

 

1. መብራት ኃይል ብቸኛው ያልተሸነፈ ቡድን ሆኗል

ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰው መብራት ኃይል በሊጉ እስካሁን ሽንፈት ያላስተናገደ ብቸኛው ቡድን መሆን ችሏል፡፡ እስከ 7ኛው ሳምንት ሳይሸነፍ የተጓዘው መከላከያ ወደ ቦዲቲ አምርቶ 1-0 በመሸነፉ መብራት ኃይል ብቸኛው ቡድን ሆኗል፡፡

በ13 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መብራት ኃይል አምና በዚህ ወቅት ካደረጋቸው የመጀመርያዎቹ 7 ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው 4 ነጥብ ብቻ ነበር፡፡

2. የወላይታ ድቻ የማሸነፍ ጉዞ

ወላይታ ድቻ በተከታታይ 4 ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ 1 አጥብቧል፡፡ ድቻ አምና ወደ ሊጉ ከመጣ ወዲህ 4 ተከታታይ ጨዋታዎችን በድል ፈፅሞ አያውቅም፡፡

አምና በተመሳሳይ የቅዱስ ጊዮርጊስን ያለመሸነፍ ጉዞ የገታው ድቻ በ1ኛው ዙር ቦዲቲ ላይ መከላከያን አስተናግዶ በተመሳሳይ 1-0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

3. ሲዳማ ደርቢ

ሲዳማ ቡና ትላንት ሀዋሳ ከነማን በማሸነፍ ሀዋሳ ላይ ያለውን ጥሩ ሪኮድ አስጠብቆ ወጥቷል፡፡ ከ2002 ጀምሮ ሀዋሳ ላይ በተካሄዱት 6 የሲዳማ ደርቢ ደርቢዎች ሲዳማ ቡና ሽንፈትን ያስተናገደው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡

የይርጋለሙ ክለብ በ2002 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ ወዲህ 11 ደርቢዎች የተደረጉ ሲሆን ሲዳማ ቡና 3 ጊዜ ሀዋሳ ከነማ ደግሞ 2 ጊዜ ድል አድርገዋል፡፡ በ6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

4. አማራ ደርቢ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ7 አመታት በኋላ በሁለት የአማራ ክለቦች መካከል የተደረገ ጨዋታ አስተናግዶ ወልድያ ከነማ ዳሽን ቢራን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ በሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ በሁለት የአማራ ክለቦች መካከል ጨዋታ የተደረገው በ2000 ዓ.ም ሲሆን ባህርዳር ላይ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በፋሲል ከነማ 2-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡

ወልድያ ከነማ በፕሪሚየር ሊግ ታሪኩ የመጀመርያ 3 ነጥቡንም ትናንት አሳክቷል፡፡

5. የቡና የአዳማ ጉዞ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ ቡና አስቸጋሪ ጉዞዎች መሃከል የአዳማ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ ቡድኑ ወደ አዳማ ተጉዞ ባደረጋቸው ያለፉት 8 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 2 ጨዋታዎችን ብቻ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሁለቱ ቡድኖች በአዳማ አበበ ቢቂላ ባደረጓቸው 12 ጨዋታዎች 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ 4 ጊዜ ኢትዮጵያ ቡና በ1994 ፣ 95 ፣ 97 እና 2003 አሸንፏል፡፡ አዳማ ደግሞ 3 ጨዋታ (1996 ፣ 2001 እና 2004) አሸንፏል፡፡

6. ሀዋሳ ከነማ በአሰልጣኝ ታረቀኝ መሪነት እያዘገመ ነው

የሁለት ጊዜ የሊግ ቻምፒዮኑ ሀዋሳ ከነማ በአሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ስር ውጤቱ መልካም እየሆነ አይደለም፡፡ አሰልጣኙ ባለፈው አመት አጋማሽ ቡድኑን ከተረከቡ ወዲህ ባደረጓቸው 20 ጨዋታዎች ሀዋሳ ከነማ ማሸነፍ የቻለው 5 ጨዋታ ብቻ ነው፡፡

ቡድኑ ያለፉትን 3 ተከታታይ ሽንፈቶች ጨምሮ ካለፉት 10 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ደካማው ወልድያ ከነማን ብቻ ነው፡፡

7. ባንክ ከ ደደቢትን የአቻ ጉዞ

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በአደኛው ዙር ባደረጓቸው 6 የእርሰ በእርስ ግንኙነቶች በአሰስገራሚ ሁኔታ ከአንዱ በቀር በ5 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደደቢት ጋር እስካሁን ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ድል ማስመዝገ የቸለው በአxንድ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡ ደደቢት በ2002 ወደ ሊጉ ካደገ ወዲህ ባደረጓቸው 11 ጨዋታዎች (የትናንቱን ጨምሮ) ደደቢት 3 ጨዋታዎችን በድል ሲፈፅም ፤ ባንክ አንድ ጨዋታ አሸንፏል፡፡ ቀሪዎቹን 7 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ፈፅመዋል፡፡

8. የክለቦች የነጥብ ተቀራራቢነት

 

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ8 ሳምንታት በኋላ በክለቦች መካከል ያለው የነጥብ መቀራረብ አስገራሚ ሆኗል፡፡ በሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና እና የመጨረሻ ደረጃን በያዘው ወልድያ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 8 ብቻ ሲሆን አሁን በለው የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት እስከ 10ኛ ያሉት ቡድኖች በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች መሪ የመሆን እድል አላቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *