መረጃዎች | 66ኛ የጨዋታ ቀን

የ17ኛ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደርጋል፤ መርሀ-ግብሮቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ አርባምንጭ ከተማ

17ኛው ሳምንት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኙ ቡድኖች በሚገናኙበት መርሀ-ግብር ይከፈታል።

በአዳማ ከተማ ውጤታማ ጊዜ በማሳለፍ ላይ የሚገኙት ምዓም አናብስት በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ከስጋት ቀጠናው ርቀዋል።

በሀያ አንድ ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት አልባ ጉዞ ከማድረጉም በተጨማሪ መረቡን ባለማስደፈር ዘልቋል። ምዓም አናብስት በአዳማ ከተማ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች አስራ አንዱን ማሳካት ችለዋል። ምንም እንኳን በመጨረሻው ጨዋታ በመጠኑ ተጋላጭ ቢሆንም በቅርብ ሳምንታት ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት የገነባው መቐለ በመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች በስድስቱ ግብ ያለማስተናገዱ ጉዳይን ስንመለከት ቡድን ስለሚከተለው ጥንቃቄ መር አጨዋወት ዓይነተኛ ማሳያ ነው።

አዳማ ከተማ ላይ ድል ባደረጉበት መርሀ-ግብር በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻሉት ምዓም አናብስት በያዙት የድል መንገድ ለመዝለቅ በፊት መስመር ላይ ያላቸው የውጤታማነት ደረጃ ከዚህም በላይ ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ያሬድ ብርሀኑ ከጉዳት መልስ ወደ ግብ ማስቆጠሩ መመለሱ ለአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬው ቡድን መልካም ዜና ቢሆንም ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ግብ ሳያስተናግድ ከወጣው የአዞዎቹ የመከላከል አደረጃጀት የሚጠብቃቸውን ፍልምያ ግን የጨዋታው ክብደት ይጨምረዋል።

በመጀመርያዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ በመያዝ ዓመቱን የጀመሩት አዞዎቹ በተከታታይ ያስመዘገቧቸው አወንታዊ ውጤቶች ደረጃቸው ከሰንጠረዡ አጋማሽ በላይ እንዲመነደግ አድርጓቸዋል።

በውድድር ዓመቱ ለሊጉ አዲስ ከሆኑት ቡድኖች የላቀ ውጤት ማስመዝገብ የቻለው ቡድኑ ካደረጓቸው አስራ አራት የሊግ ጨዋታዎች ሰባቱን በድል ሲወጣ በአንድ ነጥብ ተጋርቶ በስድስቱም ተሸንፎ በሃያ ሁለት ነጥቦች በ6ኛ ደረጃነት ተቀምጧል። በሊጉ በአንድ ጨዋታ ብቻ አቻ በመውጣት ብቸኛ የሆኑት አዞዎቹ ያስተናገዷቸው ስድስት ሽንፈቶች ወደኋላ ጎተታቸው እንጂ በሰባት ጨዋታዎች ድል በማድረግ ቀዳሚ ከሆኑት ኢትዮጵያ መድን እና ሀድያ ሆሳዕና በመቀጠል ከመቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በጋራ በርከት ያለ ድል በማስመዝገብ በሁለተኛነት መቀመጥ ችለዋል።

ሦስት ተከታታይ ድሎች ያስመዘገቡት አዞዎቹ በቅርብ ሳምንታት ከነጥብም ባለፈ በመከላከል ሆነ በማጥቃት በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛሉ።
አራት ድል እና አንድ ሽንፈት ባስመዘገቡባቸው አምስት መርሀ-ግብሮች ስድስት ግቦች ከማስቆጠር በዘለለ በሦስቱ መረባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣታቸውም ቡድኑ በጥሩ አቋም እንዳለ ማሳያ ነው። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስቆጠረው ታታሪው እና ብዙ የማይባልለት አሕመድ ሑሴን በጥሩ አቋም መገኘቱም ቡድኑን ውጤታማ እያደረገው ይገኛል።

በሊጉ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ ለቀጥተኛ አጨዋወት የሚያደሉት ምዓም አናብስት እና አዞዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ከተከታታይ ድሎች እንደመምጣታቸው እና ሙሉ ሦስት ነጥብ መውሰድ የቡድኖቹን የተፎካካሪነት መጠን ይበልጥ የሚያረጋግጥ እንደመሆኑ ጨዋታው ተጠባቂ ያደርገዋል።

በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ሸሪፍ መሐመድ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፍም።
አምበሉ ያሬድ ከበደም ቅጣቱን ቢጨርስም በዛሬ ጥዋቱ ልምምድ መጠነኛ ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በጨዋታው የመሳተፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። ከዚ በተጨማሪ ያብስራ ተስፋዬ፣ መናፍ ዐወል፣ አሸናፊ ሀፍቱ፣ አማኑኤል ልዑል እና የረዥም ጊዜ ጉዳት የገጠመው ክብሮም አፅብሐ በነገው ጨዋታ የማይሳተፉ ተጫዋቾች ናቸው። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሳሙኤል አስፈሪ ፣አበበ ጥላሁን እና አሸናፊ ተገኝ ጉዳት አሁንም ከጉዳታቸው አላገገሙም፤ በፍቅር ግዛውም በህመም ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ታውቋል።

ቡድኖቹ ሁለት ጊዜ (በ2010) ተገናኝተው በትግራይ ስቴድየም የተካሄደው እና ጋናዊው ጋይሳ አፖንግ ቢስማርክ ሀትሪክ በሰራበት ጨዋታ መቐለ 4-0 ሲያሸንፍ በአርባምንጭ የተካሄደው እና የመቐለ የመጀመርያው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ደግሞ ያለ ጎል ተለያይተዋል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ድል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በከተማቸው አስቸጋሪ የሚባልን ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎቻቸው ሽንፈት አስተናግደው አሁን ላይ በአስራ አምስት ነጥቦች ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛሉ።

አዳማ ከተማዎች በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሳምንታት ያሳዩን ብቃት ርቋቸው ይገኛል፤ ቡድኑ በመጀመርያዎቹ አምስት ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦች ይዞ ዓመቱን ቢጀምርም ከዛ በኋላ በተከናወኑ ጨዋታዎች በተከታታይ ነጥብ ጥሎ ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ለመግባት ተገዷል።
በሊጉ በጣምራ ደካማው መከላከል አደረጃጀት ባለቤት የሆኑት አዳማዎች ይህን ደካማ የመከላከል መዋቅር መፍትሄ ማበጀት ቀዳሚው የቤት ሥራቸው እንደሚሆን ይጠበቃል። ቡድኑ በቀጠናው ካሉ ቡድኖች የተሻለ የግብ መጠን ማስቆጠር ቢችልም ደካማው የመከላከል ቁመናቸው ላሉበት ዝቅተኛ ደረጃ ምክንያት የሆነ ይመስላል።

ብዙ ተጠብቆባቸው የውድድር ዘመኑን የጀመሩት ሻምፕዮኖቹ ንግድ ባንኮች በ15 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ለመራቅ ከቅርብ ተፎካካርያቸው በሚያደርጉት የነገው ወሳኝ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል።

በአዳማ ባደረጓቸው ጨዋታዎች አንድ ድል፣ ሦስት አቻ እና አንድ ሽንፈት ያስመዘገቡት ንግድ ባንኮች በቅርብ ሳምንታት በመከላከሉ ረገድ መሻሻሎች አሳይተዋል፤ በውድድር ዓመቱ አስራ አምስት ግቦች ያስተናገደ ቡድኑ መጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች በማስተናገድ በአንፃራዊ የተሻለ ቁጥር አስመዝግበዋል። ሆኖም በሰንጠረዡ ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ ለመፎካከር የግብ ማስቆጠር አፈፃፀሙን ማሻሻል ይኖርበታል። ንግድ ባንኮች ጨዋታዎቻቸውን በጥሩ ብቃት ቢከውኑም ባለፈው የውድድር ዓመት ዋነኛ ጥንካሬያቸው የነበረው የማጥቃት ጥንካሬያቸው ማጣታቸውን ተከትሎ ወደ ላይ እንዳይጠጉ ምክንያት ሆኗቸዋል፤ በነገው ጨዋታም በሊጉ ከወልዋሎ ጋር በጣምራ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስተናገደ ቡድን እንደመግጠማቸው ከፍ ያለው ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ አይገመትም።

በአዳማ ከተማ በኩል አድናን ረሻድ እና ዳግም ተፈራ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ የማይኖሩ ሲሆን ረዘም ላሉ ጊዜያት ከሜዳ ርቆ የነበረው ቢኒያም ዐይተን ግን ከጉዳቱ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት ሳይጠበቅ ከባለፈው ጨዋታ ውጭ የነበረው አማካይ ቢንያም ካሳሁን ወደ ልምምድ ተመልሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። ሌላኛው አማካይ ብሩክ እንዳለ ግን በአምስት ቢጫ ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል። እንዲሁም ፉአድ ፈረጃ እና ሱሌማን ሀሚድ ከጉዳታቸው ለማገገም ወራቶችን የሚፈልጉ በመሆናቸው ከስብስቡ ውጭ ከሆኑ ሰነባብተዋል። የተቀሩት የሀምራዊያኖቹ አባላት ለነገው ወሳኝ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

በሊጉ 34 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባንክ 17 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። አዳማ 4 ጨዋታ ሲያሸንፍ በ12 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ባንክ 56 ጎሎች ሲያስቆጥር አዳማ 29 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።