የካፍ ውሳኔ አሉታዊ እና አዎንታዊ ጎኖች …

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን [ካፍ] በሞሮኮ መዲና ራባት ማክሰኞ እና እረቡ የአፍሪካ እግርኳስን በገቢ ደረጃ ለማጠናከር ያስችላሉ ያላቸው ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ይህንን ተከትሎ ከውይይቱም በኃላ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ሃገራትን እና የሚደረግበትን ወቅት ላይ ለውጥ አድርጓል፡፡

ካፍ በአመራር ደረጃ ለውጥ ካደረገ ወዲህ ለውጦች እንደሚኖሩ ይታመን ነበር፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የመጋቢቱ የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ኮንፌድሬሽኑን ለ29 ዓመታት የመሩትን ካሜሮናዊውን ኢሳ ሃያቱ እና ደጋፊ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቶቻቸውን አሰናብቶ የ57 ዓመቱ ማዳጋስካራዊውን አህመድ አህመድን ተክቷል፡፡ ታዲያ የፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ታማኝ ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አህመድ ከወዲሁ የሃያቱ አስተዳደር ሲመራባቸው የነበሩ አካሄዶቹን ወደ መሬት ለመቅበር መዘጋጀታቸው አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ኢንፋቲኖም በአፍሪካ እግርኳስ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ አሁንም በማስቀጠል ላይ ይገኛሉ፡፡

በካፍ የፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ኢንፋንቲኖ በዚህ ጉዳይ ፈፅሞ ባይስማሙም እጃቸው ረጅም መሆኑን አሳይተዋል፡፡ በተለይ ሃያቱ በኢንፋቲኖ ጣልቃ ገብነት መጋቢት ላይ በነበረው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ምሬታቸውን አህመድ፣ የፊፋ ዋና ፃሃፊ ፋቱማ ሳሞራ እና ኢንፋንቲኖ ላይ ሲገልፁ ተስተውሏል፡፡ የ70 ዓመቱ ካሜሩናዊ የቀድሞ አትሌት በምርጫው ከተሸነፉም በኃላ ለሰላምታ እጃቸው የዘረጉት ፋቱማ ሳሞራን ከቁብ ሳይቆጥሯቸው ማለፋቸው ተከትሎ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆነው ቆይተዋል፡፡

በስምፓዚየሙ የነተሱት አብዛኞቹ ሃሳቦች ወደ ትግበራ እንዲገቡ የተደረጉት ውሳኔዎች የአውሮፓውያን ጥቅም፣ ፍላጎት እና ተፅዕኖ ከማስጠበቅ አንፃር የተደረጉ ናቸው የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡

ለውጡ አዎንታዊ ብቻ ሳይሆን አሉታዊም መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለአብነት ያህል የተወሰኑትን ውሳኔዎች ደግመን ብንመረምር ‘ገቢን ከማሳደግ’ የሚለው ቃል ተደጋግሞ ይመጣል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ካፍ የፋይናንስ አቅሙን ከማጠንከር አንፃር የወሰዳቸው እርምጃዎች እንደሆኑ ያመለክታል፡፡ የተወሰኑ ውሳኔዎች (በተለይ ስር ነቀል ለውጥ የተደረገባቸው) ያላቸውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅእኖ ከፋፍለን እንመልከት፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ የተሳታፊ ሃገራትን ቁጥር ከ16 ወደ 24 ማሳደግ

እንደአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1957 የአፍሪካ ዋንጫ ሲጀመር ሶስት ተሳታፊ (ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን) ነበሩት፡፡ ከ1996 ወዲህ የታሳፊ ሃገራት ቁጥር ወደ 16 አድጓል፡፡ በ1996 ናይጄሪያ ራሷን ከውድድሩን በማግለሏ በ15 ሃገራት መካከል ሲካሄድ በ1998 ቡርኪናፋሶ ውድድሩን ስታስተናግድ 16 ሃገራት ለመጀመሪያ ግዜ ተካፍለዋል፡፡

አዎንታዊ ጎን

56 አባል ፌድሬሽኖች ባሉበት አህጉር 16 ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫው ይሳተፋሉ፡፡ ይህም በመቶኛ ሲቀመጥ 29% ነው፡፡ አሁን ላይ የቁጥር ጭመራውን ተከትሎ 43% ይደርሳል፡፡ የቁጥሩ መጨመር እውን መሆኑን ተከትሎ እምብዛም የመሳተፍ እድል ያላገኙ ሃገራትን እድል ያሰፋል፡፡ እንደኢትዮጵያ ያሉ በማጣሪያ ውድድሮች በደካማ ጉዞ ለሚዳክሩ ሃገራት የተሳታፊ ሃገራት ቁጥር መጨመር ጥሩ ዜና ይመስላል፡፡ የተሳታፊ ቁጥር ከተጨመረ በዛው የሚደረጉ ጨዋታዎቹ ብዛትም ይጨምራል፡፡ ይህ ደግሞ ከቴሌቪዥን መብት የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ያስችለዋል፡፡ ስለዚህም የተሳታፊ ሃገራት ቁጥር መጨመር አንድም ያላየናቸው የአፍሪካ ሃገራት በውድድሩ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲያስችል ከስፖንሰር እና ቴሌቪዥን መብቶችን የሚገኘውን ገቢ በእጅጉ ይጨምራል፡፡

በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈው የማያውቁ ሃገራት የመሳተፍ እድልን ማግኘቻቸው መልካም የሆነ ጎን አለው፡፡ በተለይ እንደኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ተጫዋቾቻቸው በትልቅ ደረጃ እንዲታዩ በር ከፋች ነው፡፡ በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በውጭ ሃገር ሊጎች የመጫወት እድል ማግኘት የቻሉት እንደአፍሪካ ዋንጫ ባሉ ውድድሮች መሳተፍ በመቻላቸው ነው፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ አብዛኞቹ ከ2010 የአለም ዋንጫ አዘጋጅ ከነበረችው ደቡብ አፍሪካ እና ሰሜን አፍሪካ ሃገራት ውጪ ያሉ የአፍሪካ ሃገራት የ24 ሃገራት የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ አቅሙ ያላቸው አይመስልም፡፡ ቢሆንም በጣምራ የሚያዘጋጁ ሃገራትን በርከት ብለው እንዲኖሩ ያስችላል፡፡ ይህም ጥሩ ጎን አለው፡፡ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ ሚሊኒየም ጋና እና ናይጄሪያ እንዲሁም በ2012 ኤኳቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን በጣምራ ካስተናገዱት የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ በጣምራ የሚያዘጋጁ ሃገራት እምብዛም አይታይም፡፡ ይህም በሃገራት መካከል ያለው ግንኙነት ከማዳበሩ ባሻገር አዘጋጅ ሃገራት ለመሰረት ልማት የሚሰጡት ትኩረት ይዳብራል፡፡ ጥራት ያላቸው ስታዲየሞች የመገንባታቸው እድል ይበዛል፡፡

አሉታዊ ጎን

24 ሃገራት በአፍሪካ ዋንጫ መካፈል የሚጀምሩ ከሆነ አሁን ባለው የአፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ አቅም የማይሆን ይመስላል፡፡ ከ16 ሃገራት ይልቅ 24 ሃገራት መሳታፈቸውን ተከትሎ የስታዲየም፣ የመለማመጃ ቦታዎች እና የሆቴል አቅርቦት አሁን ባለው አህጉሪቱ አቅም ማስተናገድ የሚችሉ ሃገራት ቁጥር በጣም ውስን ናቸወ፡፡ ውድድሩን ለማስተናገደም ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ ግድ ይላል፡፡ አሁን ባለው የአህጉሪቱ አቅም ይህ የማይቻል ነው፡፡
የጨዋታዎች ጥራት ላይም ትልቅ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ተሳታፊ ሃገራት ሲጨመሩ በማጣሪያው እምብዛም ሳይፈተኑ የሚያለፉ ሃገራት ቁጥርም ይጨምራል፡፡ ስለዚህም በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በሰፊ ግብ ልዩነት የሚሸነፉ ቡድኖችም ቁጥር ይጨምራል፡፡ ጥራት ያላቸው ቡድኖች 16 ሃገር በሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መገኘታቸው ባህል ሆኗል፡፡ አሁን የመጣው የቁጥር መጨመር ይህንን ባህል እንዳያፋልስ ያሰጋል፡፡ የማጣሪያ ጉዞውንም ጣዕም እንዳያጣ ከሚያሰጉ ጉዳዮች መካከል ነው፡፡

የኬንያው ሲቲዝን ቲቪ ዘገቢ የሆነው ጄኮብ ኢሲያ በራባት የነበረውን ሲምፖዚየም በስፍራው ተገኝቶ ተከታትሏል፡፡ ጄኮብ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት የቁጥር መጨመሩ ውድድሩ ያለውን ጣዕም እንዳያጣ ይሰጋል፡፡ “በ24 ሃገራት መካከል የሚደረገው ውድድር ጣዕም አይኖረውም፡፡ የፉክክር መጠኑንም በዛው ልክ እየወረደ ነው የሚመጣው፡፡ አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ይህ መሆኑ ለእኔ ጥሩ አይመስለኝም፡፡” ይላል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ከ2019 ጀምሮ ወደ ሰኔ/ሐምሌ ወር መዛወር

የአፍሪካ ዋንጫ በጥር/የካቲት ወር ለረጅም ግዜያት መካሄዱን ተከትሎ የኢሳ ሃያቱ አስተዳደር ከአውሮፓ ክለቦች ጋር የጥቅም ግጭት ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡ በፊፋ ህግ መሰረት ደግሞ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን በብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ወቅት የመልቀቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ የጥር ወር የአብዛኞቹ የአውሮፓ ሊጎች የአንደኛ ዙር ጨዋታቸውን የሚያጠናቀቁበት እና በሊጉ ወሳኝ ወቅት የሚደርሱበት ግዜ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎም በአፍሪካ ዋንጫ የሚካፈሉ ተጫዋቾቻቸውን ላለመልቀቅ ሲያመነቱ ይስተዋላል፡፡

አዎንታዊ ጎን

ውድድሩን ከጥር/የካቲት ወደ ሰኔ/ሐምሌ መወሰዱ አፍሪካን ከሚጠቅምባቸው አንዱ አሁንም የገቢ ምንጭ ማደግ ነው፡፡ በሰኔ/ሐምሌ ወራት ላይ በአፍሪካ ተወዳጅነትን ያተረፉ የአውሮፓ ሊጎች ተጠናቀው እረፍት ላይ እንዲሁም የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት የሚጀምሩበት ወቅት መሆኑ ቢያንስ የአፍሪካ ዋንጫ የሚመለከተውን የተመልካች ቁጥር ይጨምረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህም ከገቢ አንፃር ካፍ ከተለያዩ ስፖንሰሮች እና የቴሌቪዥን መብት የሚያገኘውን ረብጣ ገንዘብ በይበልጥ ያሳድግለታል፡፡

በአውሮፓ የእግርኳስ ህይወታቸውን ለሚመሩ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች እና ክለቦቻቸው ይህ መልካም ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በብዛት ወደ ክለቦቻቸው ሲመለሱ በተለይ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የነበሩት በቀላሉ ወደ ቋሚነት ለመመለስ እና ወጥ የሆነ አቋም ለማሳየት ይሳናቸዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ወቅትም ክለቦቻቸው በምትካቸው ሌሎች ተጫዋቾችን በብዛት ማስፈረማቸው ሌላው የአፍሪካዊያን ተጫዋቾች ጭንቀት ነው፡፡ የወቅት ለውጡ ግን ክለቦችንም ተጫዋቾችንም ከዚህ ጭንቀት ይገላግላል፡፡

ብዙ አፍሪካዊያን የሚያደንቋቸው የአፍሪካ ከዋክብት ተጫዋቾችን እንዲመለከቱ ይረዳል፡፡ ውሳኔው በካፍ እና በአውሮፓ ክለቦች መካከል ያለውን ቅራኔ ስለሚፈታ በተለያዩ ሃገራት የሚጫወቱ ከዋክብቶችን በአፍሪካ ዋንጫ ለመመልከት ያስችለናል፡፡

እንደኢትዮጵያ ባሉ በዘመናዊ ፕሮግራም በማይመሩ ሃገራት የአፍሪካ ዋንጫው የወቅት ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ የውስጥ ሊግ ውድድሮቻቸውን (ዋናውን ሊግ እና ጥሎ ማለፉን) በፍጥነት እንዲያጠናቀቁ ያስገድዳል፡፡ ይህ በጎ ነው፡፡ ለምሳሌ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጠናቀቀው ሰኔ አጋማሽ ላይ ሲሆን አሁን ላይ የአፍሪካ ዋንጫው በሰኔ እንዲሁም የአፍሪካ ክለቦች ውድድር በነሃሴ እንዲጀመሩ መደረጉ ፌድሬሽኑ የፕሬግራም አወጣጡን እና አጠቃላይ ሊጉን የሚመራበትን መንገድ እንዲያጤን በእጅጉ ጫና ላይ ይከተዋል፡፡

ጄኮብ በዚህ ውሳኔ ላይ ያለውን ምልከታ እንዲ ይገልፀዋል፡፡ “በካፍ እና አውሮፓ ሊጎች መካከል ያለው ቅራኔ ማብቃት ነበረበት፡፡ ከዋክብት የሆኑ አፍሪካዊያንን በአፍሪካ ዋንጫው መመልከት እንፈልጋለን፡፡ ተጫዋቾች በሃገራቸው ጥሪ እና ቀጣሪ ክለቦቻቸው መካከል ሆነው የሚደርስባቸው ጫናን ማስቀረቱ በጎ ነው፡፡”

አሉታዊ ጎን

ሰኔ/ሐምሌ በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት የዝናብ ወቅት ነው፡፡ ጥራት ያላቸው ሜዳዎች በስፋት በማይገኙባት አፍሪካ በዝናባማ አየር ሁኔታ ጨዋታዎችን ማካሄድ እጅግ ከባድ መሆኑን ለመረዳት የሳይንስ አዋቂ መሆን አይጠይቅም፡፡ የኢሳ ሃያቱ አስተዳደር ውድድሩን ወደ ክረምቱ ወቅት ከማምጣት የተቆጠበው ዋነኛ ምክንያቱ ይህ ነው፡፡ እዚህ ላይ የአህመድ አህመድ አስተዳደር ይህንን እውነታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ መስጠቱ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡

የ24 ሃገራት የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገዱ ሙሉ አቅም አሁን ባለው ደረጃ አላቸው በሚባሉት የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ደግሞ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በክረምቱ ወቅት ይመዘገባል፡፡ ለምሳሌ በአልጄሪያ በሰኔ ወር የሙቀት መጠኑ ከ37-40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል፡፡ በከፍተኛ ሙቀት ጨዋታዎችን ማካሄድ አሁንም አስቸጋሪ ነው፡፡ አውሮፓዊያን በለውጥ ሰበብ ለረጅም ግዜ ሲመኙት የነበረውን ጥቅማቸውን በአዲሱ አስተዳደር አሳክተዋል፡፡ ይህም ካፍ ከሶስተኛ ወገን ጫና እና ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ከመላቀቅ ይልቅ ይበልጥ እጁን እየሰጠ መሆኑን አመላካች ነው፡፡

የቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የወቅት ለውጥ
የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ከነሃሴ-ግንቦት እንዲካሄድ መወሰኑ ከጉዳት ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል፡፡ የአብዛኞቹ ሃገራት የሊግ ውድድሮች የሚካሄዱት በዚሁ ወቅት መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ጥቅሙን ያጎላዋል፡፡ ከመጋቢት-ህዳር ይካሄድ በነበረው የክለቦች ውድድር የበላይነቱን የሚይዙት ክለቦች በፋይናንስ፣ አደረጃጀት እና በቡድን ስብስብ ጥራታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው፡፡ ለዚህም ማሳያ አንዲሆነን በቅርብ አመታት ውድድሮቹን ያሸነፉ ክለቦችን መመልከት በቂ ነው፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የ2016 የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ በሆነበት ወቅት ያለሟቋረጥ የሊግ፣ የጥሎ ማለፍ እና የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎችን በተጣበበ ግዜ ማካሄድ ነበረበት፡፡ ሰንዳውንስ ካለው አቅም አንፃር ይህንን ቢቋቋምም ለአብዛኞቹ አፍሪካ ክለቦች ግን ይህ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው፡፡ እንደካፍ መረጃ ከሆነ ከ70% በላይ አፍሪካ ሊጎች የሚካሄዱት ከነሃሴ-ግንቦት ባለው ግዜ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ የግዜ ለውጥ ምክንያታዊ እና ትክክለኛ ነው፡፡ የተዝረከረከ እግርኳስ አሰራር ባለባት ኢትዮጵያም ይህ ለውጥ መደረጉ ቢያንስ ፌድሬሽኑ እና ክለቦች ላይ የውስጥ ሊግ ውድድሩን የሚመሩበትን እና የሚያስኬዱበትን ኃላቀር አሰራር እንዲያሻሽሉ ጫና ሊያደርግባቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ በ2005 መጨረሻ መካሄድ የነበረበት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በ2006 ነበር የፍፃሜ ጨዋታው የተካሄደው፡፡ አሁን ላይ የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳታፊን የሚለየው ኢትዮጵያ ዋንጫ እንደቀድሞ እየተንጓተተ እንዳይካሄድ ይህ ለውጥ ፌድሬሽኑን ጫና ውስጥ ይከታል፡፡ ይህ ጠቀሜታው ፌድሬሽኑ አሁን ላይ ከመቸውም በላይ እራሱን እንዲፈትሽ ያስገድደዋል፡፡

የእድሜ ማጭበርበር

በታዳጊዎች ውድድር ላይ የአፍሪካ ሃገራት በእድሜ ማጭበርበር ይበልጥ ይታወቃሉ፡፡ በእግርኳሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ስፖርቶች በተለይም አትሌቲክስ ላይ ይህ በሰፊው ይስተዋላል፡፡ ይህን የእግርኳስ እድገት ገቺ ተግባር ለማስቆም ካፍ ዘመናዊ አካሄዶችን እንደሚከተል ውሳኔ አስፍሯል፡፡ ውሳኔው እውነትም ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ አባል ሃገራት ለወጣቶች እግርኳስ ላይ እንሰራለን ከሚሉ ጆሮ አደንቋሪ ባዶ አስተያየቶች ታቅበው ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲያመሩ ያችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የታዳጊዎች ውድድር ዋና አላማ ዋንጫ ማሸነፍ ሳይሆን ተተኪዎችን ማፍራት ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ግን የታዳጊዎች ውድድር ላይ ውጤት ፍላጋ ላይ ብቻ በማተኮር ፌድሬሽኖች እና ክለቦች በአህጉሪቱን እምቅ ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች እንዳይፈሩ እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ስለዚህም ፌድሬሽኖች እና ካፍ በእድሜ ማጭበርበር ላይ ያለቸው አመለካከት መቀየር ከቻለ የተወሰነው ውሳኔ አህጉሪቱን እግርኳስ ተስፋ እንዲያንሰራራ ያስችላል፡፡ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ካልቻለ ግን አሁንም አህጉሪቱ ጥሩ ብቃት ያላቸውን ታዳጊዎች እንዳይፈሩ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *