የካፍ ስራ አስፈፃሚ አዲሶቹ ውሳኔዎች

ሀሙስ ማምሻውን የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአፍሪካ ዋንጫ፣ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ የተወሰዱ ለውጦችን በድህረ-ገፁ ይፋ አድርጓል፡፡ ውሳኔ የተሰጠባቸው አዲሶቹ አሰራሮች

የአፍሪካ ዋንጫ

የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ በ24 ሃገራት መካከል ይካሄዳል፡፡ ውድድሩም የሚካሄድበት ወቅት ከጥር/የካቲት ወደ ሰኔ/ሃምሌ ከ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ ይዟራል፡፡ አፍሪካ ዋንጫውም በአህጉሪቱ ውስጥ ይስተናገዳል ተካፋይም ሃገሮች የአፍሪካ ሃገራት ብቻ ይሆናሉ፡፡

የክለብ ውድድሮች

ለአሁኑ በቀድሞ አሰራር እንዲቀጥል ሆኖ ከቀጣዩ አመት በኋላ ግን የክለብ ውድድሮቹ በነሃሴ ወር ጀምሮ በግንቦት ይጠናቀቃል፡፡ በቀድሞው እና አሁን ላይ አሰራር ላይ በሚገኘው ፎርማት መጋቢት ጀምሮ ህዳር ይጠናቀቃል፡፡ ውሳኔው ይህንን ያስቀራል፡፡

የወጣቶች እግርኳስ

ከ17፣20 እና 23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ ማጣሪያዎች ልክ እንደቻን በዞን ተከፋፍሎ ይካሄዳል፡፡

የእግርኳስ እድገት (አሰልጣኝነት፣ ዳኝነት እና ህክምና)

ለዳኞች የሚሰጠው ክፍያ እንዲጨምር ተወስኗል፡፡ የእድሜ ማጭበርበርን ለመግታት ሳይንሳዊ እና የህክምና መፍትሄ እንዲበጅለት በቆራጥነት ገልጿል፡፡ እንዲሁም በድንገት የሚፈጠሩ ተጫዋቾች ህልፈተ ህይወትን ለመረዳት ጥናት እንዲደረግ ኮሚቴው ወስኗል፡፡ በድንገት ህይወታቸውን እያጡ ያሉት በቅርብ ግዜያት በተለይ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ሌሎች ውሳኔዎች

ከነዚህ ውሳኔውች ሌላ ካፍ እንዳስታወቀው ከሆነ ዛምቢያ የ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ከማዘጋጀት እሯሷን አግልላለች፡፡ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫው በ2020 የጃፓኗ መዲና ቶኪዮ ለምታስታናግደው ኦሎምፒክ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ሃገራትን የሚለይ ውድድር ነው፡፡ ዛምቢያ በ2017 መጀመሪያ ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ በታሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ የሚታወስ ነው፡፡
የቻን 2018 እና የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጆች የሆኑት ኬንያ እና ካሜሮን በመስረም እና ነሃሴ ወር ዝጅግታቸው የደረበት ደረጃ እንደሚፈተሽ ካፍ ገልጿል፡፡ የተሳታፊ ሃገራት ቁጥር ከ16 ወደ 24 ማደጉን ተከትሎ ካሜሩን የማስተናገድ አቅሟ የተዳከመ መስሏል፡፡ ከራባቱ የካፍ ሲምፖዚየም በፊትም ሞሮኮ የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት ተነግሯል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ከሞሮኮ ሌላ ግብፅም ጥያቄ እንዳቀረበች የሚወጡት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ግብፅ ከወዲሁ 2018 የአፍሪካ የባህር ዳርቻ ላይ እግርኳስ ዋንጫን እንድታስተናግድ እድሉ ተሰጥቷታል፡፡
የሱዳን እግርኳስ ማህበር ቅጣት በፊፋ መነሳቱን ተከትሎ በቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የተሳተፉትን ሶስት የሱዳን ክለቦች ከውድድር ከማገድ ይልቅ ካፍ ያልተካሄደው የመጨረሻ ጨዋታቸው (ኤል ሜሪክ ከ ኤትዋል ደ ሳህል እና አል ሂላል ከፎሬቫያሪዮ ደ ቤይራ በቻምፒየንስ ሊጉ ፤ አል ሂላል አባያድ ከ ዜስኮ ዩናይትድ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ) በሽንፈት የተጠናቀቀ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህንን ተከትሎ ኤል ሜሪክ እና አል ሂላል ከምድብ ሲሰናበቱ አል ሂላል ኦባያድ ዜስኮ ዩናይትድን ተከትሎ ወደ ኮንፌድሬሽን ዋንጫው የሩብ ፍፃሜ አልፏል፡፡ ኦባያድን ተክቶ ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፍ ችሎ የነበረው የአንጎላው ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቮ ሊቦሎ ከምድብ ተሰናብቷል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ አል ሂላል ኦባያድ በሩብ ፍፃሜው ከሃያሉ የዲ.ሪ. ኮንጎ ክለብ ቲፒ ማዜምቤ ጋር ይፋለማል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *