ምርጥ 10 | በውድድር ዘመኑ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳዩ ተጫዋቾች 

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ እንደ ድክመት በተደጋጋሚ ከሚነገሩ ነገሮች መካከል እግርኳሱ ለአዳዲስ ፊቶች እድል መንፈጉ ነው፡፡ በሀገሪቱ ሊጎች ላይም በአንድ የውድድር ዘመን የምንመለከታቸው አዳዲስ ወጣቶች ቁጥር የተመናመነ ነው፡፡ ከሌሎች አመታት በተሻለ ለወጣት ተጫዋቾች እድል ተሰጥቶበታል በተባለለት የውድድር ዘመን እንኳን የተመለከትናቸው አዳዲስ ፊቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

በዛሬው የምርጥ 10 መሰናዷችን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ብቅ ካሉ እና በዘንድሮው የውድድር ዘመን ተስፋ ሰጪ አቋማቸውን ያሳዩ ተጫዋቾችን እንመለከታለን፡፡

1 ፍሬዘር ካሳ

በዘንድሮው የሊጉ ቻምፒዮን እና በአፍሪካ ውድድር መድረክ ረጅም ርቀት በተጓዘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ በዕድሜ ወጣቱ ፍሬዘር የማይረሳ የውድድር አመት አሳልፏል። ቀድሞ በመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ በመጫወት የሚታወቀው ተጨዋቹ በዘንድሮው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ቦታ ላይ ለበርካታ ጊዜያት ተሰልፎ መጫወት ችሏል። ፍሬዘር የማጥቃት ተሳትፎው ላይ ብዙ የሚቀረው ቢሆንም የመከላከል ሚናውን ግን ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በመናበብ በጥሩ ሁኔታ ሲወጣ ተስተውሏል። ከተስፋ ቡድን ካደገ በኃላ ጥሩ መሻሻል በማሳየት ከጠንካራው የቡድኑ ስብስብ ውስጥ በቦታው ቋሚ ተመራጭ ሆኖ በውድድር አመቱ መዝለቁ ተጨዋቹን በቀጣዮቹ አመታት ብዙ እንዲጠበቅበት የሚያደርግ ነው።

2 መሣይ ጳውሎስ

በወጣት ተጨዋቾች የእግር ኳስ ህይወት ውስጥ አንደኛው አስቸጋሪ ነገር በቂ የመሠለፍ ዕድልን አለማግኘት ነው። በ2008 የውድድር አመት ላይ ከተስፋ ቡድን ዋናውን ቡድን መቀላቀል የቻለው መሳይ ጳውሎስ ግን በዘንድሮው የሀዋሳ ከተማ ጉዞ ውስጥ በቂ የመሰለፍ ዕድል ማግኘት ብቻ ሳይሆን የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች እስከመሆንም ደርሷል። በተለይም ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች በሚመረጡበት የመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ የመጀመሪያ ተመራጭ መሆኑ ትልቁ ስኬቱ ነው ማለት ይቻላል። ተጫዋቹ በቦታው ከተለያዩ ተጨዋቾች ጋር ሲጫወት መቆየቱም ከፍተኛ ትኩረት እና ጥንቃቄ በሚጠይቀው የመጫወቻ ቦታው ላይ ጥሩ ልምድ እንዲያካብት መልካም ዕድል እንደፈጠረለት ይታመናል።

3 ጊት ጋት

ቁመተ መለሎው የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሊጉ በጊዜ የተሰናበተው አዲስ አበባ ከተማ የተከላካይ መስመር በጉዳት በታመሰበት ወቅት የመሰለፍ እድል ካገኘ ወዲህ ቦታውን አስከብሮ እስከ አመቱ መጨረሻ መዝለቅ ችሏል፡፡ በግሉ ድንቅ የሚባል ጊዜም አሳልፏል፡፡
ጊት ከአካላዊ ግዝፈቱ ጋር በተገናኘ የአየር ላይ ኳሶችን በማሸነፍ ስኬቱ እና የአንድ ለአንድ ግነኙነቶች ላይ ያለውን የበላይነት ልምድ ካላቸው አጥቂዎች ጋር ሲገናኝም ተመልክተነዋል፡፡ ያለውን ብቃት ጠብቆ እድገቱን ማስቀጠል የሚችል ከሆነም በቀጣይ ጥቂት አመታት ከክለብም ባለፈ ለብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት መስጠት የሚያስችል የእምቅ ችሎታ ባለቤት መሆኑን ዘንድሮ አስመስክሯል፡፡

4 አቤል እንዳለ

ደደቢት በውድድር አመቱ በቂ የጎል ዕድሎችን ለአጥቂው ክፍል የማድረስ ችግር ያለበትን የአማካይ ክፍል አሳይቶናል። ሆኖም አቤል ባገኛቸው የመሰለፍ ዕድሎች በቀጣዮቹ አመታት ይህንን የቡድኑን ችግር የማቃለል አቅም እንዳለው አሳይቷል። ኳስን በእርጋታ አቅልሎ መጫወት የሚችል እና ከተጣማሪው የአማካይ ተጨዋች ጋር በቀላሉ መግባባት የሚችል አይነት ተጨዋች ነው። አቤል በተለይ ከተከላካዮች ፊት በተክለሰውነቱ እና በአንድ ለአንድ ፍልሚያ ጠንካራ ከሆነ ተጨዋች ጋር ሲጣመር ይበልጥ በነፃነት በመጫወት ጥሩ ዕይታ እና የኳስ ማደራጀት ክህሎት ያለው በመሆኑ ይበልጥ ያለው ችሎታ ጎልቶ ይወጣል ። በ2009 የውድድር አመትም ያገኛቸው የመሰለፍ ዕድሎች እንደተጨዋች ለማደግ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩለት በመሆኑ በቀጣዮቹ አመታት በቦታው ላይ ቋሚ ተሰላፊ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው።

5 አማኑኤል ገብረሚካኤል

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ብዙዎችን ያስደመመው አማኑኤል ገብረሚካኤል መቀለ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ባደረገው ጉዞ ውስጥ ከፍተኛ ሚናን መጫወት ችሏል፡፡ በውድድር አመቱ 18 ግቦችን ከማስቆጠሩ በዘለለ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ የቡድኑ ልዩነት ፈጣሪ መሆን ችሏል፡፡ በ2008 ከዳሽን ቢራ ተስፋ ቡድን ያደገው አማኑኤል በ2010 የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ ያንጸባርቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡

6 ሱራፌል ዳኛቸው

በአዳማ ከተማ የአማካይ ክፍል ውስጥ ተፅዕኖውን በሚገባ ማሳየት የቻለው ሱራፌል በተለይም በሁለተኛው የውድድሩ አጋማሽ በቡድኑ ውስጥ የነበረው ተሳትፎ ከፍ ብሎ ታይቷል። የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና ከዛም አልፎ ግቦችን በማስቆጠር ጥሩ የውድድር አመት ያሳለፈው ሱራፌል የቴክኒክ ብቃቱ ለክለቡ ብቻ ሳይሆን ለሀገሩም የወደፊት ባለ ተስፋ ያደርገዋል። በተለይም ብዙዎቹ ጎሎች በአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ብቻ በሚቆጠሩበት ሊጋችን ውስጥ በተሰጠው እድል ተጠቅሞ ያስቆጠራቸው አራት ግቦች ከቡድኑ አጥቂዎች የግብ መጠን በአንድ ብቻ ያነሰ መሆኑ ክለቡ ካለበት አጠቃላይ የግብ ማግባት ችግር አንፃር ሲታይ ወደፊት ለቡድኑ ተጨማሪ የግብ ምንጭ የመሆን ተስፋ እንዳለው ያመለክታል ።

7 አቤል ያለው

በ2008 ሐረር ሲቲን ተቀላቅሎ ጥሩ የውድድር ጊዜን ማሳለፍ የቻለው አቤል ዘንድሮ ደደቢትን ተቀላቅሎ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ ቢችልም በመጀመሪያው ዙር የደደቢት ቆይታው በፕሪምየር ሊጉ እምብዛም የመሰለፍ እድልን ማግኘት ሳይችል ቀርቷል፡፡
በሁለተኛው የውድድር አጋማሽ ወደ ፋሲል ከተማ ማቅናት የቻለው አቤል ተስፈኛ አጥቂነቱን በአጼዎቹ ቤት ማሳየት ችሏል፡፡ ጥሩ የግብ አስቆጣሪነት ደመነፍስ እና በተለያዩ የአጥቂ ሚናዎች የመጫወት ብቃት ያለው አቤል የቀጣዮቹ አመታት ኮከብ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ የውድድር ዘመን አሳልፏል፡፡

8 አቡበከር ነስሩ

በውድድር ዘመኑ አጋማሽ አወዛጋቢ ከነበረ ሒደት በኃላ ሐረር ሲቲን ለቆ ኢትዮጵያ ቡናን መቀላቀል የቻለው አቡበከር ቡድኑ ባደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ባሳየው ድንቅ ብቃት በርካቶች ማስደመም ችሏል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተሰለፈበት ጨዋታ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ በሲዳማ ቡና 3-1 ሲሸነፍ የቡድኑን ብቸኛ ግብ ማስቆጠርም ችሎ ነበር፡፡ ቦታ አያያዙ ፣ በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያለው መረጋጋት እና የአጨራረስ ብቃቱ የወደፊቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ተስፋ ያደርገዋል፡፡

9 ቡልቻ ሹራ

የአዳማ ከተማው አጥቂ አምና ወደ ዋናው ቡድን ካደገ ወዲህ በተሰጠው እድል ተጠቅሞ ወሳኝ ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ለብሔራዊ ቡድንም እስከመመረጥ ደርሶ ነበር፡፡ ይህም ተጫዋቹ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በቋሚነት ቡድኑን የሚጠቅምበት እድል ያገኛል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ እንደተጠበቀው ከአምናው የተሻለ የመሰለፍ እድል ባያገኝም በሚሰለፍባቸው ጨዋታዎች ላይ በማጥቃቱ ረገድ ደካማ በሆነው አዳማ ከተማ በተለይ ከዳዋ ሁቴሳ ጋር ሲሰለፍ በርካታ የግብ እድሎችን በመፍጠር አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሲያበረክት ተስተውሏል፡፡

10 ፍቃዱ ደነቀ

ከተስፋ ቡድኑ ያደገው ፍቃዱ ደነቀ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በመጀመሪያው ዙር እምብዛም የመሠለፍ እድልን ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ሆኖም ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ በርካታ ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት የመሰለፍ እድልን ማግኘት ችሏል፡፡
በመሀል ተከላካይ እና በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው ፍቃዱ ከንግድ ባንክ ጋር ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመውረድ ቢገደድም እንደመጀመርያ የውድድር ዘመኑ በግሉ ስኬታማ የሚባል አመት ማሳለፍ ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *