የሴቶች ዝውውር | እፀገነት ብዙነህ ደደቢትን ተቀላቀለች  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግራ መስመር ተከላካይ የነበረችው እፀገነት ብዙነህ ለደደቢት ለመጫወት በዛሬው እለት ፊርማዋን አኑራለች፡፡

በውድድር ዘመኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ ቡድን ደከም ያለ እንቅስቃሴን ቢያስያም በግሏ ከሌሎች በሊጉ ላይ ከሚጫወቱ የመስመር ተከላካዮች በተለየ ከመከላከል እንቅስቃሴ በዘለለ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በጉልህ የሚታይ እገዛ ማድረግ ችላለች፡፡ ከክለቡ ጋር የነበራት ውል መጠናቀቁን ተከትሎም ወደ ደደቢት ልታመራ እንደምትችል ሲነገር ቆይቷል፡፡

የእፀገነት ቡድኑን መቀላቀል ለቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ይጠቀሙት በነበረው የ3-5-2 ቅርፅ በመስመር ተመላላሽነት (Wing-Back) ቦታ ላይ መጫወት ከመቻሏ በተጨማሪ እንዲሁ የቡድኑ ስብስብ በጉልህ ይጎድለው የነበረውን የተፈጥሮአዊ የመስመር ተከላካይ ክፍተትን በመድፈን ለአሰልጣኙ በ4 ተከላካይ የመጫወትን አማራጭ ትፈጥራለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እፀገነትን ጨምሮ 5 አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ደደቢት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የሆነችው ብርቱካን ገብረክርስቶስን ለተጨማሪ ሁለት አመታት ውሏን አድሷል፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ ከዚህ በኃላ ምንም አይነት ተጨማሪ አዲስ ተጫዋች እንደማያስፈርም አስታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *