“የህዝቡ እና ብዙሀን መገናኛው እገዛ ያስፈልገናል” አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከሱዳን ጋር ስለሚደረገው ጨዋታ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስተያየታቸውን ስጥተዋል፡፡

ስለ ዝግጅት

ዝግጅታችን መልካም ነው፡፡ ለዚህ ይረዳን ዘንድ ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገናል፡፡ ደካማ እና ጠንካራ ጎናችንንም አይተንበታል፡፡ ለጨዋታው ያለን ዝግጁነት በአጠቃላይ መልካም ነው ብዬ አስባለው፡፡ በተጫዋቾቼ ላይ ትልቅ መነሳሳት እና ተስፋ ሰጪ ነገርም ተመልክቻለሁ፡፡

ስለ ጨዋታው

ኢትዮጵያዊ ሲባል ከማሸነፍ ውጪ ያለ ውጤትን አይቀበልም፡፡ ሁልጊዜ አንደኛ መሆንን ነው የሚፈልገው፡፡ ይህም አትሌቶቻችን የማሸነፍን ስሜት ያስተማሩን ስለሆነ እኛም በደማችን ውስጥ ያለው ያ ነገር ነው፡፡ እኔም ሆንኩ ተጫዋቾቼ የሀገራችንን ባንዲራ ከፍ ማድረግ ነው አላማችን፡፡

በአሰልጣኙ እና ፌዴሬሽኑ መካከል አለ ስለሚባለው ክፍተት

ግንኙነታችን መልካም የሚባል ነው፡፡ የተጠየኩትን ጥያቄ ጥሩ ነው ብዬ ማለፍ እፈልጋለው፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫ ያለመስጠት ጉዳይ

እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም በኔ በኩል ስራ ላይ ትኩረት ስለማደርግ ስልኬንም በአብዛኛው እዘጋዋለሁ፡፡ ስለ ራሴ ይህንን ነው ማለት የምፈልገው ፤ ሌላውን ጉዳይ ግን ፌዴሬሽኑ ምላሽ ይስጥበት፡፡

ከነገው የመጀመሪያ ጨዋታ ምን እንጠብቅ?

አሁንም መናገር የምፈልገው ማሸነፍ የውዴታ ግዴታችን ነው፡፡ ህዝቡ ከጎናችን ከሆነ እናሸንፋለን፡፡ ስለዚህ ሜዳ ላይ ውጤት ይዘን ከመውጣት ወደ ኃላ አንልም፡፡ ፈጣሪ ከፈቀደ ተጫዋቾቼ ጥሩ ነገር ይሰራሉ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን በጣም ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ካሉ ጠንካራ ቡድኖችም አንዱ ነው፡፡ በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑ ክለቦችም መገኛ ነው፡፡ ይህን ሁላችንም ልንረዳው ይገባል፡፡ ሆኖም ከነሱ ጋር የምናደርገው ጨዋታ በቀላሉ እጅ የምንሰጥበት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሜዳ ላይ የሚደረገውን መስዋትነትን ሁሉ ለመክፈል ተዘጋጅተናል፡፡ ተጫዋቾቼም ለዚህ በጣም ቁርጠኛ ናቸው፡፡

በቡድኑ ውስጥ 19 ተጫዋቾች ብቻ መያዛቸው የሚፈጥረው ክፍተት

ልክ ነው ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ይህም የሚሆንበት የራሱ የሆነ ችግሮች አሉበት፡፡ ባለፈው የፈለኩትን ያህል ተጫዋቾት አልሰበሰብኩም፡፡ በዝግጅት ጊዜ ደግም አሁን ቡድኖች በመበተናቸው የፈለኩትን ለማግኝት አልቻልኩም፡፡ 16 ተጫዋቾች 3 ግብ ጠባቂ ነው በቡድኔ ውስጥ ያካተትኩት፡፡ ታደለ መንገሻንም መርጠነው ነበር ፤ በጣም እንደሚጠቅመንም እናውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ልምምድ ላይ ባጋጠመው ጉዳት በፍሬው ተተክቷል፡፡ ዞሮ ዞሮ ከብዛት ጥራት ይሻላል የሚል አስተሳሰብ አለን፡፡ ያሉት ተጫዋቾችም መልካም ናቸው፡፡ ብዙ ቁጥር ቢኖረን ደስ ይለን ነበር ፤ ሁለት ሶስት ተጫዋቾች ከሀገር ውጭ የመጫወት እድል ለማግኘት በመጓዛቸው የሉም፡፡ ሌላው በጤና እና በተለያዩ ምክንያቶች ማካተት አልተቻለም ፤ ጠርተናቸውም አልመጡልንም፡፡ ሆኖም ባሉን ልጆች እስከ መጨረሻው እንሄዳለን፡፡

ስለ ተጋጣሚያቸው

የሱዳን ብሔራዊ ቡድን በጣም ጠንካራ ነው፡፡ በተለይ በመስመር ላይ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ጠንካራ ናቸው፡፡ ታክቲካልም ዲሲፕሊንድ ናቸው፡፡ በፍጥነት ያጠቃሉ ፣ በፍጥነት ይደራጃሉ ፣ የተጠና ኳስ ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብን ስንዘጋጅ ነው የቆየነው፡፡ በጨዋታው የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ደጋፊያችንም እንደ አስራ ሁለተኛ ተጫዋች ነው ብዬ መናገር እችላለው፡፡ የህዝቡ እና ብዙሀን መገናኛው እገዛ ያስፈልገናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *