የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የዛሬ ውሎ በውዝግብ የታጀበ ጨዋታ አስተናግዷል

የደቡብ ክልል ካስቴል ዋንጫ በሀዋሳ መካሄዱን ቀጥሎ አርባምንጭ ከወልዲያ አቻ ሲለያዩ በውዝግብ የታጀበው የሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ተቋርጦ በፎርፌ ተጠናቋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ 0-0 ወልዲያ

አስቀድም 7:30 የተጀመረውና ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል፡፡ በ3ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አበራ ከፍፁም ቅጣት ምት ጨረር ላይ አክርሮ የመታት ኳስ ደረጀ አለሙ ያወጣበት የጨዋታው ቀዳሚ ፈጣን ሙከራ ነበረች፡፡ ከሶስት ደቂቃ በኋላ ደግም ወልዲያዎች ተመሳሳይ ሙከራን በበድሩ ነርሁሴን አማካኝነት አድርገው ሲሳይ ባንጫ አውጥቶበታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ቀዳሚ የግብ እድል በመፍጠር አርባምንጮች ቀዳሚ ነበሩ፡፡ አስጨናቂ ፀጋዬ ያሻገራትን ኳስ ገ/ሚካኤል ያዕቆብ በግንባሩ ገጭቶ የወጣችበት ፤ በወልዲያ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው እና ጥሩ የተንቀሳቀሰው ያሬድ ብርሀኑ ያመቻቸውን ኳስ አንዷለም ንጉሴ ሞክሮ ወደ ውጭ የወጣችበት ለግብ የቀረቡ ነበሩ፡፡ ወልዲያዎች በሰለሞን ገ/መድህን ፤ አርባምንጮች በላኪ ሳኒ ያገኘቸው ሁለት ግልፅ ግብ የሚሆኑ አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ 1-1 ሲዳማ ቡና (ሲዳማ በፎርፌ አሸናፊ ሆኗል)

ድሬዳዋ ከተማን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በከባድ ዝናብ ጀምሮ በከባድ ወዝግብ ተቋርጧል፡፡8 ቢጫ ካርድ የተመዘዘበት እና 3 የድሬዳዋ ከተማ ተጨዋቾች በቀይ ካርድ የወጡበት ጨዋታ ከፍተኛ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ፣ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔወች እና የተጫዋቾች ያልተገባ ባህሪን አስተናግዷል፡፡ 21 ያህል ደቂቃ ተቋርጦ ዳግም ተጀምሮ ከ6 ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ተቋርጦም ሲዳማ ቡና በፎርፌ አሸናፊ እንዲሆን ተወስኗል፡

በጨዋታው ድሬዳዋ ከተማዎች በተለይ በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መሪ መሆን የቻሉበትንም ጎል ገና በ2ኛው ደቂቃ በሐብታሙ ወልደ አማካኝነት አግኝተዋል፡፡ ጨዋታው በሁለቱም በኩል መልካም እንቅስቃሴ እና የጎል ሙከራዎች እየተደረጉ ቀጥሎ በ40ኛው ደቂቃ ላይ ፌድራል ዳኛ አብርሀም ኮይራ የድሬዳዋ ከተማው አማካይ ኢማኑኤል ላርያ አፀያፊ ስድብ ተሳድበሀል በሚል በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥቶታል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በድሬዳዋ 1-0 መሪነት ተገባዷል፡፡

ከዕረፍት መልስ ለ16 ደቂቃዎች ጨዋታው ተደርጎ በተነሳ ግርግር 21 ደቂቃ የተቋረጠ ሲሆን ከድሬዳዋ ከተማ በኩል ሁለት ተጨማሪ ቀይ ካርድ ታይቷል፡፡ በተለይም ሱራፌል ዳኛቸው አስቀድሞ ቢጫ ካርድ ተመልክቶ የነበረ ቢሆንም ፌድራል ዳኛ አብርሀም ኮይራ ቢጫ ካርዱን ባለመመዝገቡ ምክንያት በድገሚ ቢጫ ካርድ አሳይቶ እንዲቀጥል ሲያደርግ ሲዳማዎች ተቃውሞ በማስነሳታቸው ዋና ዳኛው ከአራተኛ ዳኛ ጋር ከተነጋገሩ በኃላ ሱራፌል በቀይ ካርድ ወጥቷል፡፡ እንደገና ከሁለት ደቂቃ ቆይታ በኃላ ጨዋታው ሊጀምር ሲል የመሀል ዳኛው አብርሀም ኮይራ ያሬድ ዘውድነህን በቀይ ካርድ ሲያስወጣ ተቃውሟቸውን ያሰሙት የድሬዳዋ ተጫዋቾች አንጫወትም በሚል ጨዋታውን አቋርጠው ወጥተዋል፡፡

በዳኞች እና በአዘጋጅ ኮሚቴው አባላት ጥረት የድሬዳዋ ተጫዋቾች በድጋሚ ወደ ሜዳ ገብተው ጨዋታው ዳግም ተጀምሯል፡፡ ሲዳማ ቡናም የተጫዋቾችን በቀይ መውጣት በመጠቀም የአቻነቱን ጎል ለማግኘት ያደረገው ጥረት ተሳክቶ በአዲስ ግደይ አማካኝነት አቻ መሆን ችሏል፡፡ ሆኖም ከጎሉ መቆጠር በኋላ የድሬዳዋ ከተማዎቹ ዮሴፍ ዳሙዬ እና አህመድ ረሺድ ተጎድተናል ብለው ከሜዳ በመውጣታቸው እና በጨዋታ ህግ ከ7 በታች ተጫዋቾች የያዘ ቡድን ጨዋታውን መቀጠል የማይችል በመሆኑ ሊቋረጥ ችሏል፡፡ ሲዳማ ቡናም በፎርፌ አሸናፊ በመሆን ወደ ግማሽ ፍጻሜ መሸጋገሩን አረጋግጧል፡፡

በጨዋታው የዳኝነት ክፍተት የጨዋታውን መንፈስ ወደ አላፈላጊ ግርግሮች እንዲያመራ አስተዋፅኦ ከማድረጉ ባሻገር በስፍራው የነበሩ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች የሚሰነዝሯቸው አጸያፊ ስድቦች እንዲሁም የአዘጋጅ ኮሚቴው በቅንጅት ስራዎችን የመስራት ችግር በጉልህ የተስተዋለበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል፡፡ ከምንም በላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅትን ከመለካት የዘለለ ፋይዳ በሌለው ጨዋታ እንዲህ ያሉ የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈቶች መታየታቸው በእግርኳሱ ላይ የተንሰራፋውን ችግር አጉልቶ ያሳየ ሆኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *