​ሪፖርት | የሙሉአለም ረጋሳ ብቸኛ ግብ ለሀዋሳ ሶስት ነጥቦች አስገኝታለች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 1-0 በማሸነፍ በሜዳው ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። አንጋፋው ሙሉአለም ረጋሳም ተቀይሮ በገባ በ3 ደቂቃ ውስጥ ልዩነት ፈጣሪዋን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

እጅግ ከወትሮው በተለየ መልኩ ጥቂት ተመልካች በታደመበት ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ ሙሉ በሙሉ የጨዋታ የበላይነት ሲወስድ ድሬዳዋዎች በአንፃሩ ደካማ እንቅስቃሴን ያሳዩበት ነበር፡፡

የመጀመሪያውን የግብ አጋጣሚን በመፍጠር ሀዋሳ ከተማ ቀዳሚው ነበር። ደስታ ዮሀንስ ከመዐዘን ምት ያሻማውን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ የወጣችበት ሙከራ፡፡  በ20ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን በግል ጥረቱ ወደ ሳጥን ውስጥ እየገፋ ገብቶ የመታትን ኳስ ሳምሶን አሰፋ አውጥቶበታል፡፡ በድጋሚ ከአንድ ደቂቃ በኃላ ፍሬው ሰለሞን ያገኛትን መልካም አጋጣሚን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ አሁንም በድሬዳዋ ላይ የእንቅስቃሴ የበላይነት መውሰድ የቻሉት ሀይቆቹ በ32ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ በቀኝ መስመር ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ የሰጠውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ወደ ግብ ቢመታም ኢላማወመን ሳትጠብቅ ወደ ላይ ወጥታለች፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ  ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ፍሬው ሰለሞን ያገኛትን ኳስ ግብ ጠባቂው ተመስገን ዳባ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡

41ኛው ደቂቃ ሳምሶን አሰፋ በመጎዳቱ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በተመስገን ዳባን ግብ ጠባቂነት የተጫወቱት ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ሱራፌል ዳንኤል ከመስመር ያሻማውን ኳስ ከጉዳት የተመለሰው ሀብታሙ ወልዴ በቀጥታ መቶ ኢላማውን ሳትጠብቅ ከወጣችበት ሙከራ ውጪ በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ የጎል እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉአለም ረጋሳን ቀይረው በማስገባት የጀመሩት ሀዋሳዎች በዚህኛውም አጋማሽ የበላይ ነበሩ። 48ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን በግራ መስመር በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ ወደ ግብ ሞክረሮ ግብ ጠባቂው ተመስገን ዳባ ሲተፋው ሙሉአለም ረጋሳ አግኝቶ ወደ ግብነት በመቀየር ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላም ሀዋሳዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን በ68ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን የሰጠውን ኳስ ተጠቅሞ ደስታ ዮሀንስ ሁለተኛ ግብ አስቆጠር ሲባል ወደ ላይ የሰደዳት ፣ 79ኛው ደቂቃ ላይ ፍርዳወቅ ሲሳይ ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ያልፀደቀው ጎል ፣ 85ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋአብ ዮሴፍ የድሬዳዋ ተከላካዮችን አልፎ የሰጠውን ኳስ በእለቱ ምርጥ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ መትቶ ግብ ጠባቂው ተመስገን ያወጣበት ሀዋሳዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በጨዋታው ላይ የሚታይ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት ድሬዳዋዎች በዚህ የጨዋታ አጋማሽ መደበኛ ደቂቃ መገባደጃ ድረስ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በጭማሪ ሰአት ዮሴፍ ዳሙዬ በግል ጥረቱ ተጫዋቾችን አልፎ ያቀበለውን ኳስ ዘላለም ኢሳያስ ከግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ ድሬዳዋን በስተመጨረሻ አንድ ነጥብ ልታስገኝ የምትችል ነበረች።

ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥቡን 10 በማድረስ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ በ7 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

” በሜዳችን እንደመጫወታችን ማሸነፍ የግድ ይለን ነበር። ዛሬ የተለየ አጨዋወት እና አቀራረብ ነበረን። እጅግ ጥሩ አጋጣሚን መፍጠርም ችለናል። በሁለተኛው አጋማሽ ዊሊያም ስለ ተጎዳብን ሙሉአለምን አስገብተናል። ልምድ አለው ይጠቅመናል ብለን ስላሰብን አስገብተነው ግብ አስቆጥሮልናል። ውጤትም ይዘን ወጥተናል።

” ተጋጣሚያችን አቻ ለመሆን የፈለጉ ይመስላሉ። እኛ ደግሞ ባገኘነው ቀዳዳ ማስቆጠር ስለበረብን ያንን አድርገናል። ”


ዘላለም ሽፈራው – ድሬዳዋ ከተማ
“ጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር። ከዛ በኃላ አቅማችንን ስለምናውቀው ሜዳውም ሙሉ ደቂቃ ላይ እንደፈለከው ለመጫወት ስለማያስችል ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ለማድረግ ነበር ጥረት ያደረግነው። በመጀመሪያው አርባ አምስት ተሳክቶልን ወጥተናል።

” የገባብን ጎል የግብ ጠባቂያችን ችግር ነው። በሱ አልፈርድም። በሁለተኛው አጋማሽ አጥቅተን ለመጫወት አስበን ነበር። ሆኖም መጨረስ አልቻልንም። የተጎዱ ተጫዋቾች ቢኖሩም ፍፁም ለኛ ሜዳው አልተመቸንም። ልጆቼም ሜዳው አላጫወተንም ነበር ያሉኝ። የሳሚ መጎዳት የተወሰነ ጫና ውስጥ ከቶናል በቀጣይ ጨዋታ ተሻሽለን እንቀርባለን የሚል ሀሳብ ነው ያለኝ።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *