ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ| ጅማ አባ ቡና መሪዎቹን ተጠግቷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እና አንድ የተስተካካይ መርሐ ግብር ዛሬ ተከናውነው ጅማ አባቡና መሪዎቹን ሲጠጋ ደቡብ ፖሊስ እና ሀላባ ከተማ ነጥብ ጥለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ደርቢ ጅማ አባቡና ከፋ ቡናን አገናኝቶ ባለሜዳው ጅማ አባ ቡና 4-0 አሸንፏል። ቴዎድሮስ ታደሰ ሐት-ትሪክ በሰራበት ጨዋታ ጅማዎች በሜዳቸው ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሱበት ነበር። ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል በፈጣን እቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን የጎል ሙከራ መደረግ የተጀመረው ገና በመጀመሪያው ደቂቃ የአባቡናው ኪዳኔ አሰፋ ከግራ መስመር ከተመስገን የተሻገረለትን ወደግብ ሞክሮ ሰይቡ ሀብታሙ እንደምንም አውጥቶበታል። በ4ኛው ደቂቃ የከፋ ቡናው ትዕዛዙ በግምት ከ 25 ሜትር አካባቢ አክርሮ የወጣበት በከፋ ቡናዎች በኩል አስደንጋጭ ሙከራ ነበር። በ20ኛው ደቂቃ በከፋ ቡና ግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታደሰ ወደ ግብነት በመቀየር ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኃላ መረጋጋትና ትኩረት ችግር የታየባቸው ከፋ ቡናዎች ሁለተኛ ግብ ለማስተናገድ ደቂቃዎች አልፈጀባቸውም። በ23ኛው ደቂቃ ከ16:50 ውጭ በግራ ጠርዝ ላይ ኪዳኔ አሰፋ አክሮ የመታው ወደግብነት በመቀየር አባቡና በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለተኛ ግባቸውን አስቆጥረዋል። በ41ኛው ደቂቃ በኃይሉ በለጠ ከተመስገን የሻገረለትን ኳስ ሲያድነው በ45ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ሀይደር እና ጀሚል በአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ በመግባት ሀይደር የሞከረውን ሰይቡ ሀብታሙ ቢያድነውም የተተፋውን ኳስ ቴዎድሮስ አስቆጥሮ በ3ለ0 መሪነት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ጅማ አባቡናዎች በይበልጥ ተጭነው ለመጫወት እንዲሁም ከፋ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ ላለማስተናገድ አፈግፍገው አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ወደ አባቡና የግብ ክልል ለመድረስ ሞክረዋል። በአባቡናዎች በኩል ከ46ኛው ደቂቃ ጀምሮ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በአጥቂው ቴዎድሮስ የሚሳቱት ኳሶች የባለሜዳዎቹ በሰፋ የጎል ልዩነት ማሸነፍ የሚያስችሏቸውን አጋጣሚ በተደጋጋሚ ሲያመክን ነበር። በ61ኛው ደቂቃ ከዳዊት ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን በማስቆጠር ለራሱ 3ኛውን ለቡድኑ 4ኛውን ግብ አስቆጥሯል። ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጥንቃቄ አጨዋወትና ቅያሪዎችን በማድረጋቸው ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ያለ ግብና በእቅስቃሴ ረገድ ከኳስ ቁጥጥር ውጭ እብዛም የነበረ ሲሆን ጨዋታው በጅማ አባቡና የ4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

መሪው ደቡብ ፖሊስ እና ተከታዩ ሀላባ ከተጋጣሚዋቻቸው ጋር  ነጥብ ተጋርተዋል። በ22ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ወደ ነገሌ ያመራው ሀላባ ከተማ በ15ኛው ደቂቃ በስንታየው መንግስቱ ግብ መሪ መሆን ቢችሉም በ45ኛው ደቂቃ አሰፋ ሳላድ ለነገሌ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሮ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ወደ ወራቤ ያቀናው መሪው ደቡብ ፖሊስም ከስልጤ ወራቤ ያደረገውን ጨዋታ ያለግብ አጠናቋል።

ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ሻሸመኔን 2-1ማሸነፍ ሲችል ቤንች ማጂ መሰለ ወልደሰማያት በ88ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ቡታጅራ ከተማን 1-0 አሸንፏል። ወልቂጤ ከተማ ከ ዲላ ከተማ ሊደረግ የነበረው ጨዋታ በጣለው ዝናብ ምክንያት ሳይከናወን ቀርቷል።