ዮሃንስ ሳህሌ የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ሆነዋል

ያለፈውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን በመቐለ ከተማ ያሳለፉት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ማምራታቸው ታውቋል፡፡ አሰልጣኙ ስማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ከቻምፒዮኑ ጅማ አባ ጅፋር ጋር ተያይዞ ሲነሳ ቢቆይም ምርጫቸው ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያው ክለብ ሆኗል፡፡

ማክሰኞ ጠዋት አሰልጣኝ ዮሃንስ ወደ ጅማ አባ ጅፋር አምርተው ክለቡን ይረከባሉ ተብሎ ቢጠበቅም የሃሳብ ለውጥ ማድረጋቸውን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር ድርድር በማድረግ ቀጥሯቸዋል፡፡ አሰልጣኝ ዩሃንስ በድሬዳዋ ከተማ የ1 ዓመት ውል መፈረማቸውም ታውቋል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ የውድድር ዓመቱን በከፍተኛ በጀት ብዙ ተጨዋቾችን አዛውሮ ቢጀምርም የውጤት ቀውስ ውስጥ ገብቶ ላለመውረድ በመታገል ነበር የጨረሰው፡፡ ክለቡ በቀጣዩ አመት ተጠናክሮ ለመምጣት በማሰብ የአሰልጣኝ ለውጥን ምርጫው ያደረገ ሲሆን ቡድኑን በግዜያዊነት ሲመሩት የነበሩት አሰልጣን ስምኦን አባይ ምትክ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና መቐለ ከተማ አሰልጣኝ ዮሃንስ ተሹመዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ አዲስ አዳጊውን ክለብ መቐለ ከተማን አራተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቀቅ ከረዱ በኃላ ውላቸው በመጠናቀቁ ነበር የሰሜን ኢትዮጵያውን ክለብ የለቀቁት፡፡